ቀጥታ፡

ዘንድሮ በሰሜን ሸዋ ዞን በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር ከ36 ሺህ ሔክታር በሚልቅ መሬት ላይ ችግኝ ይተከላል

ደብረ ብርሃንሚያዝያ 22/ 2018 (ኢዜአ)፡- በመጪው ክረምት በሚካሄደው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር 36 ሺህ ክታር በሚልቅ መሬት ላይ ችግኝ እንደሚተከል የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ አስታውቋል።

ለመጪው ክረምት አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር የሚተከሉ 294 ሚሊየን ችግኞች እስካሁን መዘጋጀታቸውን በመምሪያው የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ቡድን መሪ ጌታነህ ተ/ማርያም ገልጸዋል።


 

በቀሪ ወራትም ፈጥነው የሚደርሱ ችግኞች ላይ በማተኮር የማዘጋጀት ሥራው እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

በአጠቃላይም በመጪው ክረምት ከ36 ሺህ 260 ሔክታር በሚልቅ መሬት ላይ ችግኞች እንደሚተከሉ ለኢዜአ ተናግረዋል።

ከአሁን በፊት የተተከሉ ችግኞች አርሶ አደሩን በእንስሳት ዕርባታና ማድለብ፣ በንብ ማነብ፣ በመኖ አቅርቦትና በሌሎች የሥራ ዘርፎች በማሰማራት ጥምር ግብርናን ለማስፋፋት ምቹ ሁኔታ ፈጥረዋል ብለዋል።

በዞኑ ባለፉት ዓመታት የለሙ 1 ሺህ 163 ተፋሰሶች የአፈር ለምነትን በማሻሻል፣ የገጸና ከርሰ ምድር ውኃን በማበልጸግና ለመስኖ ልማት በማዋል የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ማሳደጋቸውንም አክለዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም