የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ተገቢ ምላሽ እንዲያገኝ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች መጠናከር አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ተገቢ ምላሽ እንዲያገኝ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች መጠናከር አለባቸው
ጂንካ፤ ሚያዝያ 22/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ተገቢ ምላሽ እንዲያገኝ በንቅናቄ የተጀመረው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን አስገነዘቡ።
ኢትዮጵያ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ የባሕር በር የማግኘት መብት እንዳላት በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ምስክር ከተማ ለኢዜአ አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት የትውልዱ ጥያቄ ሆኖ በአደባባይ እየተነሳ ያለው የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ፤ የሀገርን ብሔራዊ ደኅንነት ከማስጠበቅ ባለፈ በቀጣናው ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማስፈን ያስችላል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ያለሕግ አግባብ በፖለቲካ ሴራ የተነጠቀችውን ወደብ መልሳ እንድታገኝ የተጀመረው በመርኅ ላይ የተመሠረተ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት መጠናከር እንዳለበት መክረዋል።
የባሕር በር አለመኖር ከሀገር ደኅንነትና ሁለንተናዊ ዕድገት ጋር ስለሚያያዝ አጀንዳ ሊሆን ይገባል ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ጌታቸው ብርሃኑ ናቸው።
ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የኢትዮጵያን እውነታ ከማሳወቅ ባለፈ ምሁራንን ያሳተፈ ጥምረት ፈጥሮ ሳይንሳዊ መረጃና ማስረጃዎችን መሠረት ያደረገ ሐሳብ የሚንሸራሸርበት መድረክ መፍጠር እንደሚገባም ጠቁመዋል።
አጀንዳው ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የዘርፉ ምሁራንም ኅብረታቸውን በማጠናከር የሕብረተሰቡን ንቃተ-ኅሊና ማሳደግና የኢትዮጵያን እውነታ ለዓለም የሚያስገነዝቡ ሥራዎችን መሥራት አለበን ብለዋል።