ቀጥታ፡

የፓርቲዎች ክርክርና የምረጡኝ ቅስቀሳ የፖሊሲ አማራጮች ላይ ማተኮር አለበት - ምሁራን

ወልቂጤ፤ሚያዝያ 22/2018 (ኢዜአ)፡-የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክርና የምረጡኝ ቅስቀሳ ለሃገር በሚበጁ ሃሳቦችና የፖሊሲ አማራጮች ላይ ማተኮር እንዳለበት ምሁራን ገለጹ፡፡

ግንቦት 24/2018 ዓ.ም ለሚካሔደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ክልላዊና ሃገራዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመገናኛ ብዙሀን፣ በጎዳና ላይ እና በተለያዩ አማራጮች ክርክርና የምረጡን ቅስቀሳ እያካሄዱ ነው።

ፓርቲዎችና የግል ዕጩ ተወዳዳሪዎች በመገናኛ ብዙሃን አማራጭ ሃሳቦችን ማቅረባቸው ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጉልህ ድርሻ እንዳለው ምሁራኑ አመልክተዋል፡፡

የተፎካካሪ ፓርቲዎቹ ክርክርና የምረጡኝ ቅስቀሳ ለሀገር በሚበጁ ሃሳቦችና የፖሊሲ አማራጮች ላይ ማተኮር እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡

የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፋሪስ ደሊል (ዶ/ር) እንደገለፁት፤ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ክርክሮችና ቅስቀሳዎች ካለፉት ምርጫዎች በተሻለና ህዝብን ባከበረ መልኩ እየተካሄደ ነው።

በምርጫ ቅስቀሳው ወቅት ለሀገር በሚበጁ ሀሳቦችና የፖሊሲ አማራጮች ላይ ማተኮር አለባቸው ብለዋል።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ኢንጂነር ቀነኒ ኤልያስ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በመገናኛ ብዙሃን እየተደረገ ያለው የምርጫ ቅስቀሳና ክርክር ፓርቲዎቹ የያዙትን አማራጭ ሃሳብ ለመራጩ ህዝብ ግልፅ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ፓርቲዎቹ ልማትና አብሮነት ላይ ያተኮረ የፖሊሲ አማራጮችን በማቅረብ ለሀገር በሚጠቅሙ ሃሳቦች ላይ ማተኮር እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡

ፓርቲዎች በቅድመ ምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ሀገርን ቀዳሚ የሚያደርጉና ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስጠብቁ ተጨባጭ ሀሳቦችን ማንሳት እንዳለባቸው የጠቀሱት ደግሞ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ መምህርና ተመራማሪ እድሜዓለም ተመስገን ናቸው።

የወለጋ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ስለሺ ታመነ (ዶ/ር) በበኩላቸው ፤ፓርቲዎቹ ኢትዮጵያን መንግስት መስርተው ሊመሯት የሚችሉት አንድነቷና ሰላሟ ሲጠበቅ መሆኑን በመገንዘብ ፍፁም መከባበርና መቻቻልን መርህ አድርገው ሊንቀሳቀሱ ይገባል ብለዋል፡፡

#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም