በኦሮሚያ ክልል ባለፉት 9 ወራት ከ2 ሚሊየን ለሚልቁ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል ባለፉት 9 ወራት ከ2 ሚሊየን ለሚልቁ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል
አዲስ አበባ፤ 22/2018 (ኢዜአ)፡- ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ2 ሚሊየን ለሚልቁ ዜጎች በሀገር ውስጥና በውጭ የሥራ ዕድል መፈጠሩን የኦሮሚያ ክልል የሥራ ዕድል ፈጠራና ክኅሎት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዋሲሁን ጎልጋ ገለጹ።
ለ4 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች የሥራ ፈጠራ ሥልጠና መሰጠቱንም ገልጸዋል።
ከእነዚህ መካከልም ፍላጎት ያላቸውን 2 ነጥብ 6 ሚሊየን ወጣቶች በመለየት በሥራ ዓለም ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በኩል የክኅሎት ማሳደጊያ ሥልጠና እንዲያገኙ መደረጉን ለኢዜአ ተናግረዋል።
ከዞን እስከ ቀበሌ ድረስ ያሉትን ተጨባጭ ሁኔታዎች መሠረት በማድረግ፤ በኢንዱስትሪ፣ በግብርና እና በአገልግሎት ዘርፎች የተለዩ የሥራ ዕድሎች መፈጠራቸውንም አስረድተዋል።
ይህ የሥራ ዕድል ፈጠራ ሂደትም በክኅሎት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን በማድረግ ዜጎች በየመስካቸው ውጤታማ እንዲሆኑ መሠራቱን አረጋግጠዋል።
በበጀት ዓመቱ 2 ሚሊየን 720 ሺህ ዜጎችን በማደራጀትና በቅጥር የሥራ ዕድል ለመፍጠር መታቀዱን ጠቁመው፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሀገር ውስጥ ለ2 ሚሊየን 17 ሺህ 208 ዜጎች እንዲሁም 159 ሺህ ዜጎች በውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል።
ለሥራ ዕድል ተጠቃሚዎቹ ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር አንጻርም፤ 95 ሺህ ሄክታር መሬት ለማምረቻ፣ ከ7 ሺህ በላይ የመሸጫ ሼዶች እንዲሁም ከ23 ቢሊየን ብር በላይ የፋይናንስ አቅርቦት መመቻቸቱን ተናግረዋል።
ወደ ሥራ የገቡ ዜጎች ለሚያመርቷቸው ምርቶች ሰፊ የገበያ ትስስር እንዲፈጠር መደረጉን ገልጸው፤ በዚህም ውጤታማ የሆኑ 1 ሺህ 800 ኢንተርፕራይዞች ወደ ኢንቨስትመንት ደረጃ እንዲሸጋገሩ መደረጉን ገልጸዋል።