ቀጥታ፡

ለሀገር ዕድገትና ልማት ይበጃል የምንለውን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል-ተማሪዎች

ሐረር፤ሚያዝያ 22/2018(ኢዜአ)፦ ለሀገር ዕድገትና ልማት ይበጃል የምንለውን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል ሲሉ በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የጤናና ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ ተማሪዎች ተናገሩ።

በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ይበጀናል የሚሉትን ፓርቲ ለመምረጥ ልዩ የመመዝገቢያ ድረ ገጽን በመጠቀም ምዝገባ ማካሄዳቸውንም ገልጸዋል።

ከተማሪዎቹ መካከል በኮሌጁ የ3ኛ ዓመት ተማሪ መክሊት ሻውል እንዳለችው ምርጫ ቦርድ ባዘጋጀላቸው ልዩ የመመዝገቢያ ድረ ገጽን በመጠቀም ይበጀኛል የምትለውን ፓርቲ ለመምረጥ መመዝገቧን ገልጻለች።

"ለምርጫ ስመዘገብ የመጀመሪያዬ ነው" ያለችው ተማሪዋ ለሀገር ይጠቅማል፤እኔንም ይወክለኛል የምለውን ፓርቲ እመርጣለሁ ብላለች።

ሌላው የኮሎጁ የ3ኛ ዓመት የላቦራቶሪ ቴክኒሺያን ተማሪ ሙርቴሳ ዲኒ ይህንን እድል ተማሪዎች በማግኘታችንም እድለኛ ነን ብሏል።

የአራተኛ ዓመት የፋርማሲ ተማሪ አሚራ መኪ በበኩሏ፥ ለሀገር ዕድገትና ልማት ይበጃል የምትለውን ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀቷን ተናግራለች።

በኮሌጁ የተማሪዎች ህብረት ፕሬዝዳንትና የአምስተኛ ዓመት የህክምና ሳይንስ ተማሪ አድናን አብዱሰላም ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳና ልዩ የመመዝገቢያ ድረ ገጽ በመጠቀም ተማሪዎች ባሉ አማራጮች ሁሉ እንዲመዘገቡ እያደረግን እንገኛለን ብሏል።

በአሁኑ ውቅትም ልዩ የመመዝገቢያ ድረ ገጽን በመጠቀም ተማሪዎች እየተመዘገቡ እንደሚገኙም ተናግሯል።

#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም