ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና አዲስ አበባ ከተማ የሚያገናኘው መርሐ ግብር ተጠባቂ ነው 

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 22/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 23ኛ ሳምንት ዛሬ ይጠናቀቃል። 

ከቀኑ 9 ሰዓት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከአዲስ አበባ ከተማ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይጫወታሉ።


 

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ57 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው። አዲስ አበባ ከተማ በ11 ነጥብ 13ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

የወቅቱ የሊጉ የዋንጫ ባለቤት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካሸነፈ መሪነቱን ያጠናክራል።

አዲስ አበባ ከተማ በ22ኛ ሳምንት በቦሌ ክፍለ ከተማ 1 ለ 0 ተሸንፏል። ጨዋታውን ማሸነፍ ቡድኑ ላለመውረድ በሚያደርገው ፉክክር ወሳኝ ሶስት ነጥብ ያስገኝለታል።

በሌላኛው መርሐ ግብር ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከይርጋጨፌ ቡና ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ57 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል። ይርጋጨፌ ቡና በ17 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ማሸነፍ ኢትዮ ኤሌክትሪክን በዋንጫ ፉክክሩ እንዲቆይ ያደርገዋል። 

ባለፉት ሁለት የሊግ ጨዋታዎች ያሸነፈው ይርጋጨፌ ቡና ከወራጅነት ስጋት ለመላቀቅ ሶስት ነጥብ ያስፈልገዋል።

ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ ቦሌ ክፍለ ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ ይጫወታሉ።

ቦሌ ክፍለ ከተማ በ37 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል። ድሬዳዋ ከተማ በ24 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። 

ቦሌ ክፍለ ከተማ ካሸነፈ ተከታታይ ሶስተኛ ድሉን ያስመዘግባል።

በአንጻሩ በ22ኛ ሳምንት በይርጋጨፌ ቡና የ1 ለ 0 ሽንፈት ያስተናገደው ድሬዳዋ ከተማ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም