ነገሌ አርሲ ከፋሲል ከነማ ጋር ይጫወታሉ - ኢዜአ አማርኛ
ነገሌ አርሲ ከፋሲል ከነማ ጋር ይጫወታሉ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 22/2018 (ኢዜአ):- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 29ኛ ሳምንት ዛሬ አራት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።
ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ነገሌ አርሲ ከፋሲል ከነማ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ነገሌ አርሲ በ44 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል። ተጋጣሚው ፋሲል ከነማ በ42 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
አዲስ አዳጊው ነገሌ አርሲ ባለፉት ሶስት የሊግ ጨዋታዎች አቻ ወጥቷል። ፋሲል ከነማ በ28ኛ ሳምንት በመቀሌ 70 እንደርታ የ3 ለ 0 ሽንፈት አስተናግዷል።
ሁለቱም ቡድኖች ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርጉት ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።
በሌላኛው መርሐ ግብር ኢትዮጵያ ቡና ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ኢትዮጵያ ቡና በ41 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃን ይዟል። ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በ32 ነጥብ 17ኛ ደረጃን በበመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ከቀናት በፊት በ20ኛ ሳምንት ተስተካካይ መርሐ ግብር ቅዱስ ጊዮርጊስን 3 ለ 1 ያሸነፈው ኢትዮጵያ ቡና ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይጫወታል።
ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በ28ኛ ሳምንት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 2 ለ 0 አሸንፏል። ሁለቱም ቡድኖች በድል ጉዟቸው ለመቀጠል ይፋለማሉ።
ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ አርባምንጭ ከተማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
አርባምንጭ ከተማ በ24 ነጥብ የመጨረሻውን 20ኛ ደረጃን ይዟል። ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ34 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
የሊጉ ግርጌ ላይ የሚገኘው አርባምንጭ ከተማ ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች አላሸነፈም።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፉት ሁለት የሊግ ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግዷል። ሁለቱም ቡድኖች ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ይፋለማሉ።
ሀዲያ ሆሳዕና ከመቀሌ 70 እንደርታ ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ።
በ34 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሀዲያ ሆሳዕና ባለፉት ሁለት የሊግ ጨዋታዎች አቻ ወጥቷል።
ተጋጣሚው መቀሌ 70 እንደርታ በበኩሉ በ29 ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። ቡድኑ ባለፉት ሁለት የሊግ ጨዋታዎች ድል ቀንቶታል።
ሀዲያ ሆሳዕና ወደ ድል ለመመለስ፣ መቀሌ 70 እንደርታ ደግሞ የማሸነፍ ጉዞውን አጠናክሮ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት ይጫወታሉ።