ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ትሮፊ 2026 የዞን 5 ውድድርን ታስተናግዳለች

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 21/2018 (ኢዜአ)፦ የ2026 የዓለም አቀፍ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን (IHF) ትሮፊ የዞን 5 የምስራቅ አፍሪካ ውድድር ሚያዝያ 26 ቀን 2018 ዓ.ም በኢትዮጵያ አዘጋጅነት በአዲስ አበባ  ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ እና የምስራቅ አፍሪካ እጅ ኳስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ፍትህ ወልደሰንበት (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ውድድሩ ኢትዮጵያን ጨምሮ በ10 ሀገራት መካከል ከ17 ዓመት በታች (Youth) እና ከ19 ዓመት በታች (Junior) ይደረጋል።

በውድድሩ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ታንዛኒያ፣ ጅቡቲ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ እና ሱዳን ይሳተፋሉ።

በሁለቱም የዕድሜ ክልል አንደኛ የሚወጡት ሀገራት ቀጥታ ለአህጉራዊው የአፍሪካ ውድድር የሚያልፉ ይሆናል።

የውድድሩ ዝግጅት በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን እና በኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ እየተመራ ሲከናወን የቆየ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ዝግጅቱ መጠናቀቁ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድኖች ሆቴል ገብተው ዝግጅታቸውን እያደረጉ ይገኛሉ።

ቡድኑ እንደ ባለፈው ዓመት አሸናፊ በመሆን ለአፍሪካ ውድድር ለማለፍና ታሪክ ለመሥራት ዝግጁ ነው ሲል የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር መረጃ በመረጃው አመልክቷል።

ስፖርታዊ ሁነቱ የኢትዮጵያን የማስተናገድ አቅም የሚያሳይ መሆኑንም ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም