በአማራ ክልል በቴክኖሎጂ የተደገፈ የኩነቶች ምዝገባ ሥርዓትን በማጠናከር የተገልጋዩን እርካታ ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል በቴክኖሎጂ የተደገፈ የኩነቶች ምዝገባ ሥርዓትን በማጠናከር የተገልጋዩን እርካታ ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል
ባህር ዳር፤ ሚያዚያ 21/2018(ኢዜአ)፦ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የኩነቶች ምዝገባ ሥርዓትን በመተግበር የተገልጋዩን እርካታ የማሳደግ ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የአማራ ክልል የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ አገልግሎት አስታወቀ።
የክልሉ የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ አገልግሎት ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ያለማውን የኩነቶች መመዝገቢያ ሲስተም ዛሬ ተረክቧል።
የአገልግሎቱ ኃላፊ ወይዘሪት መዓዛ በዛብህ በርክክቡ ወቅት እንደገለጹት የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ አገልግሎትን ውጤታማ ለማድረግ ዲጂታል ቴክኖሎጂ መጠቀም አስፈላጊ ነው።
ለዚህም ተቋሙ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለምቶ ዛሬ የተረከበው የኩነት መመዝገቢያ ሲስተም መሰረታዊ ጉዳይ ነው ብለዋል።
አሁን ላይ የለማው የኩነት መመዝገቢያ ሲስተም የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባን ዲጂታላይዝድ በማድረግ ለተገልጋዩ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችልም ተናግረዋል።
ቴክኖሎጂው ስራውን ከማቀላጠፍ ባሻገር ጥራት ያለው መረጃን ለተጠቃሚው ማህብረሰብ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያግዘው አስረድተዋል።
ይህም በክልሉ በተመረጡ 477 የምዝገባ ጣቢያዎች ሲስተሙ ቀደም ብሎ ተግባራዊ ተደርጎ ሲፈተሽ መቆየቱንም አመልክተዋል።
በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለትራንስፖርት፣ ለወረቀት፣ ለህትመትና ሌሎች ወጪዎች ይወጣ የነበረን 11 ሚሊዮን ብር ማዳን ተችሏል ብለዋል።
በቀጣይም አገልግሎቱ በቴክኖሎጂ የተደገፈውን የኩነቶች ምዝገባ ስርአትን በማጠናከር የተገልጋዩን እርካታ ማሳደግ ላይ አተኩሮ እንደሚሰራ አንስተዋል።
የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት መንገሻ አየነ (ዶ/ር) በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በምርምርና ሌሎች ተግባራት ተወዳዳሪነትቱን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ለዚህም የክልሉን ተቋማት ዲጂታላይዝድ ለማድረግ ከክልሉ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ጋር በመተባበር የጀመረውን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።
እስካሁንም ለተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና የመንግስት ተቋማት ሲስተም በማልማትና በመዘርጋት ሥራቸውን ለማቀላጠፍ የሚያስችል ሥራ መስራቱን ተናግረዋል።
የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ ደመቀ ቦሩ በዩኒቨርሲቲው የለማው የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ ሲስተም በዕቅድ ላይ የተመሰረተ ክልላዊ ልማት ለማካሄድና ፖሊሲና ስትራቴጂን ለማውጣት ያግዛል ብለዋል።