ቀጥታ፡

በክልሉ ኢንተርፕራይዞችን ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር የተከናወኑ ተግባራት ውጤት አስገኝተዋል

ሆሳዕና፤ ሚያዝያ 21/2018(ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ኢንተርፕራይዞችን በመደገፍና በማብቃት ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተስፋ ሰጪ ውጤት ማስገኘታቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለፁ፡፡

የክልሉ ስራ እድል ፈጠራ ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ "የኢንተርፕራይዞች ሽግግር ለእመርታዊ እድገት" በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጀው አውደ ርዕይና ባዛር እንዲሁም የሞዴል ኢንተርፕራይዞች ደረጃ ሽግግር እውቅና መርሃ ግብር በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል፡፡


 

ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት በክልሉ ኢንተርፕራይዞችን በማብቃት ወደ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለማሸጋገር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተስፋ ሰጪ ውጤት አስገኝተዋል።

ኢንተርፕራይዞቹ ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካትና ለውጪ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ከማምረት በተጨማሪ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል እየፈጠሩ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።


 

በክልሉ ተወዳዳሪ ኢንተርፕራይዞችን ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የክልሉ ስራ እድል ፈጠራ ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ኃላፊ ሙስጠፋ ኢሳ ናቸው።


 

በገጠርና በከተማ በአነስተኛና መካከለኛ አምራች ዘርፍ ከ25 ሺህ በላይ ኢንተርፕራይዞች በተለያዩ መስኮች መሰማራታቸውን ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ዘጠኝ ወራት በክልሉ በጥቃቅንና አነስተኛ ደረጃ የሚገኙ 4ሺህ 948 ኢንተርፕራይዞችን የማሸጋገርና 495 ሞዴል ኢንተርፕራይዞችን የመለየት ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።

አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል በሆሳዕና ከተማ የሚገኘው የጡማ ፕላስቲክ ፋብሪካ ዋና ስራ አስኪያጅ ሰለሞን ታሪኩ እና የእንጨትና የብረታብረት ማምረቻ ኢንተርፕራይዝ ሰብሳቢ ወጣት ዘርፍነሽ ሽብሩ የደረጃ ሽግግሩ ድርጅቶቻቸው ስራቸውን በተጠናከረ ሁኔታ እንዲከውኑ ማስቻሉን ጠቁመዋል።

ፋብሪካው ከ120 ሚሊየን ብር በላይ ካፒታል ማስመዝገቡንና ከ150 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል መፍጠሩን አቶ ሰለሞን ተናግረዋል።

ወጣት ዘርፍነሽ በበኩሏ ኢንተርፕራይዙ 10 ሚሊየን ብር ካፒታል ማስመዝገቡን ገልጻ 30 ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል ፈጥሯል ብላለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም