ቀጥታ፡

አምባሳደር ያለው አባተ በሕይወት ዘመናቸው ሀገርና ሕዝብን በቅንነትና በታማኝነት አገልግለዋል-ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የቀድሞ አፈ-ጉባዔ አምባሳደር ያለው አባተ በሕይወት ዘመናቸው ሀገርና ሕዝብን በቅንነትና በታማኝነት ማገልገላቸውን የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ገለጹ፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የቀድሞ አፈ-ጉባዔ አምባሳደር ያለው አባተ ረታ ሥርዓተ ቀብር በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴደራል ቤተ-ክርስቲያን ተፈጽሟል፡፡

በሥርዓተ ቀብራቸው ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህን ጨምሮ የፌደራልና የክልል መንግሥታት ከፍተኛ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶችና ወዳጅ ዘመዶቻቸው ተግኝተዋል።

የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በስርዓተ ቀብራቸው ወቅት፤ አምባሳደር ያለው አባተ በሕይወት ዘመናቸው ሕዝብን በቅንነትና በታማኝነት ያገለገሉ ትሁትና ብርቱ ሰው ነበሩ ብለዋል፡፡

ችግርን በጥበብ የሚሻገሩ እና ለአዳዲስ የፈጠራ ስራዎች ዘወትር የሚተጉ እንደነበሩም አውስተዋል፡፡

አምባሳደር ሆነው ባገለገሉበት ዘመንም አርዓያነት ያለው ተግባር ማከናወናቸውን አመላክተዋል፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር፤ አምባሳደር ያላው አባተ ከባለሙያነት እስከ ከፍተኛ ሀገራዊ ኃላፊነት የሕዝብን ጥቅምና ፍላጎት እያስቀደሙ የማይረሱ አሻራቸውን ያሳረፉ ታላቅ ሰው እንደነበሩ  ገልጸዋል፡፡

ለሁላችንም ሕይወታቸው መምህር ተግባራቸው ደግሞ ትምህርት ነበር ብለዋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ አማረ ሰጤ በበኩላቸው፡ አምባሳደር ያለው አባተ ሥራን በመርህ የሚመሩና ከሁሉም ሰው ጋር እኩል የሚግባቡ ሰው እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡

አምባሳደር ያለው አባተ ቤተሰባቸውን በመምራት አርዓያ የሆኑ ሀገር ወዳድ እንደነበሩ የተናገሩት ደግሞ ባለቤታቸው ወይዘሮ  ደስታ ዘውዴ ናቸው፡፡

መንግሥት ለሀገር ያበረከቱትን አስተዋጽኦ በማሰብ በህመማቸውና በሥርዓተ ቀብራቸው ወቅት ላሳየን አጋርነት ከልብ እናመሰግናለን ብለዋል፡፡

አምባሳደር ያለው አባተ ከአባታቸው አቶ አባተ ረታ እና ከእናታቸው ወይዘሮ ተዋበች ፋንታሁን በቀድሞው ወሎ ክፍለ ሀገር በራያ እና ቆቦ አውራጃ ቆቦ ወረዳ ጉብዬ ከተማ መጋቢት 10 ቀን 1946 ዓ.ም ተወለዱ፡፡

አምባሳደር ያለው አባተ የከፍተኛ ትምህርታቸውን በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ተከታትለዋል።

በሥራ ሕይወታቸውም ከባለሙያ ጀምሮ በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች ማገልገላቸውን የሕይወት ታሪካቸው ያሳያል።

በአመራርነት ደረጃም የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤነትን ጨምሮ በተለያዩ የክልሉ ቢሮዎች በኃላፊነት አገልግለዋል። 

በፌዴሬሽን ምክር ቤት ለሦስት ዓመታት ገደማ በአፈ ጉባኤነት የሰሩ ሲሆን በብራዚል የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ሀገራቸውን አገልግለዋል።

አምባሳደር ያለው አባተ ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ሚያዝያ 19 ቀን 2018 ዓ.ም በ72 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም