ቀጥታ፡

ፌዴራል ፖሊስ የወንጀል መከላከልና የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ስኬታማ ተግባራትን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 21/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የወንጀል መከላከልና የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ስኬታማ ተግባራትን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈፃጸም ሪፖርትን ገምግሟል።


 

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ጠቅላይ አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በሪፖርታቸው፤ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ዓለምአቀፍ ዕውቅና ያስገኙ የወንጀል መከላከል ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል።

በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ከፍተኛ ወንጀል የሚፈጽሙ አካላትን በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን በኮንትሮባንድ መከላከል፣ ቁጥጥር፣ ሕገ-ወጥ የገንዘብና አደንዛዥ ዕፅ ዝውውር የወንጀል መከላከል ዘርፍም ስኬታማ ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል።

በወንጀል ምርመራ፣ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር፣ የሽብር ወንጀል መከላከል ዘርፍም የማድረግ አቅምን በማሳደግ ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን አንስተዋል።

በሰው ሀብት ልማትና ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመታጠቅም በአፍሪካና በዓለምአቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነቱ እየጨመረ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ኮሚሽኑ ኢትዮጵያዊ መልክ እንዲላበስ፣ የዜጎችን ሰብአዊ መብት የጠበቀ የወንጀል ምርመራ እንዲያካሂድና የአሰራር አቅሙን በማሳደግ የምርመራ መዝገብ አፈጻጸሙን ማሳደግ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

መንግሥታዊና ሕዝባዊ በዓላትም ያለ ምንም የጸጥታ ስጋት እንዲከበሩ ማስቻሉን ተናግረዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት የኮሚሽኑን የዕቅድ አፈፃጸም ሪፖርት በመገምገም በሂደቱ የታዩ ጥንካሬና ክፍተቶችን በአስተያየትና ጥያቄ መልክ አቅርበዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በወንጀል መከላከልና የወንጀል ተጠያቂነትን ለማስፈን የተገኙ ስኬቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።


 

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል መላኩ ፈንታ በኮሚሽኑ ከአፍሪካ ቀዳሚ የሚያደርጉና አለምአቀፍ ተወዳዳሪነትን የሚያሳድጉ ዘመኑ የደረሰበት ቴክኖሎጂዎች መተግበራቸውን ተናግረዋል።

የስማርት ፖሊስ ስቴሽን ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ተግባራዊ መደረጉን ገልጸው፤ የቴክኖሎጂውን ተደራሽነት ለማስፋፋት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ማህበረሰቡ ወንጀሎችን መጠቆም የሚችልበት ቴክኖሎጂ ተግባራዊ በመደረጉ በሺዎች የሚቆጠሩ ጥቆማዎች መቅረባቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የትራፊክ አደጋን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በቴክኖሎጂ የታገዙ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ጠቅሰዋል፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ እፀገነት መንግሥቱ፤ ፌዴራል ፖሊስ በወንጀል መከላከልና ተጠያቂነትን በማስፈን ስኬታማ ተግባራትን እያከናወነ ነው ብለዋል።

ፌዴራል ፖሊስ ተቋማዊ ግንባታንና ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ የሚሰራቸውን ስራዎች አጠናክሮ እንዲቀጥልና የወንጀል መከላከል ተግባራትን በማህበረሰቡ ተሳትፎ ለማጎልበት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዓለም አቀፍ ሁነቶችና በዓላት በሰላም እንዲጠናቀቁ በማድረግ ለሀገሪቱ የገጽታ ግንባታ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በሰው ሀብት አቅም ግንባታና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ለውጦችን በማስቀጠል የወንጀል ተጠያቂነት የማስፈንና የወንጀል መከላከል ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በተለይም የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት አስተማማኝ በሆነ ሁኔታ ለመጠበቅ የጀመራቸውን የሪፎርም ሥራዎች አጠናክሮ እንዲቀጥል አስገንዝበዋል።

#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ #ENA

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም