በጋምቤላ ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ3 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ3 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ
ጋምቤላ፤ ሚያዝያ 21/2018 (ኢዜአ)፡- በጋምቤላ ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከተለያየ የገቢ አርዕስት ከ3 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ቸንኮት ዴቪድ ገለጹ።
በተያዘው የበጀት ዓመት ከተለያየ የገቢ አርዕስት ከ7 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ግብ ተጥሎ እየተሠራ መሆኑን ኃላፊው ለኢዜአ ተናግረዋል።
በዚህም መሠረት ባለፉት ዘጠኝ ወራት በክልሉ የነበሩ ፈተናዎችን በመቋቋም ከቀጥታ ታክስ፣ ቀጥታ ካልሆኑና ከሌሎች የገቢ አርዕስት ከ 3 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን አረጋግጠዋል።
ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከ1 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ ብልጫ አለው ብለዋል።
የተጀመሩ የገቢ አሰባሰብ ተግባራትን በማጠናከር ዓመታዊ ዕቅዱን ለማሳካት ርብርብ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
ግብር መክፈል ሕዝቡ የሚፈለገውን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሠረተ-ልማቶችን ለማሟላት ያለው ፋይዳ የጎላ በመሆኑ፤ ዜጎች የሚጠበቅባቸውን ግብር በመክፈል ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።