ቀጥታ፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የቀድሞ አፈ-ጉባዔ አምባሳደር ያለው አባተ ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመ

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 21/2018 (ኢዜአ)፦የፌዴሬሽን ምክር ቤት የቀድሞ አፈ-ጉባዔ አምባሳደር ያለው አባተ ረታ ሥርዓተ ቀብር በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴደራል ቤተ-ክርስቲያን ተፈጽሟል፡፡

በሥርዓተ ቀብራቸው ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር፣የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህን ጨምሮ የፌደራልና የክልል መንግሥታት ከፍተኛ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶችና ወዳጅ ዘመዶቻቸው ተግኝተዋል።


 

ከአባታቸው አቶ አባተ ረታ እና ከእናታቸው ወይዘሮ ተዋበች ፋንታሁን በቀድሞው ወሎ ክፍለ ሀገር በራያ እና ቆቦ አውራጃ ቆቦ ወረዳ ጉብዬ ከተማ መጋቢት 10 ቀን 1946 ዓ.ም የተወለዱት አምባሳደር ያለው አባተ የከፍተኛ ትምህርታቸውን በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ተከታትለዋል።

በሥራ ሕይወታቸውም ከባለሙያ ጀምሮ በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች ማገልገላቸውን የሕይወት ታሪካቸው ያሳያል።

በአመራርነት ደረጃም የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤነትን ጨምሮ በተለያዩ የክልሉ ቢሮዎች በኃላፊነት አገልግለዋል።


 

በፌዴሬሽን ምክር ቤት ለሦስት ዓመታት ገደማ በአፈ ጉባኤነት የሰሩ ሲሆን በብራዚል የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ሀገራቸውን አገልግለዋል።

አምባሳደር ያለው አባተ ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ሚያዝያ 19 ቀን 2018 ዓ.ም በ72 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም