ቀጥታ፡

በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ባለማነው የፍራፍሬ ችግኝ ተጠቃሚነታችን አድጓል-አርሶ አደሮች

ሃዋሳ ፤ ሚያዝያ 21/2018 (ኢዜአ)፦ በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ያለሙት የፍራፍሬ ችግኝ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እንዳሳደገላቸው በሲዳማ ክልል የሸበዲኖ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ፡፡

በሲዳማ ክልል የሸበዲኖ ወረዳ አርሶ አደሮች ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ያለሙት የፍራፍሬ  ችግኞች  አድገው  ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እንዲያረጋግጡ እያስቻሉ ነው፡፡

በወረዳው የፉራ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር መሃመድ ቦጋለ እና አርሶ አደር ሄርቲሞ ሬቢሶ የቡና ችግኝ በማልማት ውጤታማ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡


 

ችግኞቹን በኩታ ገጠም በመትከል፣ የተፈጥሮ አፈር ማዳበሪያ በማዘጋጀትና ለጥላ የሚሆን እንሰት በመትከል ተገቢውን እንክብካቤ እያደረጉ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር አቮካዶን ጨምሮ ለምግብነት የሚውሉ ፍራፍሬዎችን በማልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ በአቮካዶ ልማት የተሳተፉት አርሶ አደር ሙሴ በቴሾ ናቸው፡፡


 

ላለፉት ስምንት ዓመታት ሁለት ሄክታር በሚጠጋ ማሳቸው ላይ የተሻሻሉ ዝርያ ያላቸው የአቮካዶ ችግኞችን ተክለው በማልማት ምርቱን ለኢንዱስትሪ ፓርኮች እንደሚሸጡም አክለዋል።

የወረዳው እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ጽህፈት ቤት የቡና ፍራፍሬና ቅመማ ቅመም ባለሙያ አቶ ደሞዜ ሌዳሞ እንዳሉት በወረዳው በዘንድሮው ዓመት ከ726 ሄክታር በላይ መሬት ላይ የቡና ችግኝ ለመትከል ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል።


 

በተለይም ቡና በክላስተር በማልማት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተሰራው ስራ ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ቡናን ጨምሮ ለፍራፍሬና ለምግብት ለሚውሉ ችግኞች ትኩረት መሰጠቱን የገለጹት ደግሞ የሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ መምሩ ሞኬ ናቸው፡፡


 

በመርሃ ግብሩ ከሚተከሉ ችግኞች መካከል 60 በመቶ የሚሆኑት ለምግብነት የሚውሉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በመርሃ ግብሩም አቮካዶ፣ አፕልና ሌሎች ፍራፍሬዎችን ጨምሮ ለእንስሳት መኖም ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል፡፡

በክልሉ ለዘንድሮ ዓመት የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከ322 ሚሊዮን በላይ ችግኖች የተዘጋጁ ሲሆን በቡና ችግኝ ተከላ የተጀመረው መርሃ ግብር እስከ መጪው ሃምሌ ወር እንደሚከናወንም አስረድተዋል፡፡  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም