ቀጥታ፡

ለጠቅላላ ምርጫው የፖሊሲ አማራጫችንን ለህዝቡ በነጻነት እያስተዋወቅን ነው- የፖለቲካ ፓርቲዎች

ሚዛን አማን፣ሚያዝያ 21/2018 (ኢዜአ):-በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ፖሊሲና ፕሮግራማቸውን ለህዝቡ በነጻነት እያስተዋወቁ መሆናቸውን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።

ኢዜአ ያነጋገራቸው በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለ7ኛ ጠቅላላ ምርጫ የፖሊሲ አማራጫቸውን በነጻነት እያስተዋወቁ መሆኑን ገልጸዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ የቤንች ሸኮ ዞን ፀሐፊ መምህር ብርሃኑ ገብረመድኅን በምርጫ ሂደቱ በሰለጠነ መንገድ ለሕዝብ አማራጭ ሀሳባቸውን እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የምርጫ ሕግና ሥርዓትን ጠብቀን የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ሕዝቡ ማኒፌስቷችንን በግልጽ እንዲረዳው እያደረግን ነው ብለዋል።

በቅስቀሳ ወቅት ወደ ሕዝቡ ቀርቦ ሀሳብን ማካፈልና የፓርቲ አቋምን ማሳወቅ መራጮች በምርጫ ጊዜ ሳይቸገሩ የሚፈልጉትን ሀሳብ የያዘ ፓርቲ እንዲመርጡ ያስችላል ሲሉም አክልዋል።

ከሰላም ለኢትዮጵያ ጥምረት ፓርቲ የካፋ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ሕብረት ሰብሳቢ አቶ ቦጋለ ኃይሌ በበኩላቸው፥ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የተፈጠረውን አስቻይ ሁኔታ በመጠቀም ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በየምርጫ ክልሉ በመንቀሳቀስ የቅስቀሳ ሥራ እያከናወኑ መሆኑን ገልጸው፥ የፓርቲው እጩዎችም ከኅብረተሰቡ ጋር በቅርበት የመወያየትና ሀሳባቸውን የመሸጥ ተግባርን እያከናወኑ ነው ብለዋል።

በሚዲያ እየተደረጉ ያሉ የክርክር መድረኮች ለመራጩ ህዝብ በሀሳብ የበላይነት መንግስት መመስረት ላይ የበኩሉን እንዲወጣ መሰረት የሚጥል መሆኑን ጠቁመዋል።

በቅስቀሳ እና በክርክር መድረኮች የምርጫ ህጉን አክብረው ማኒፌስቷቸውን ለመራጮች በማድረስና የፓርቲያቸውን አቋም በማንጸባረቅ ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ከትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ፓርቲ የእናት ፓርቲ ሚዛን ማዕከል ፀሐፊ አቶ ወንድማገኝ ወልደጊዮርጊስ፤ የምርጫውን ፍትኃዊነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን ተናግረዋል።

ለተግባራዊነቱም የምርጫ ህጉን ተከትለው የፖለቲካ አቋማቸውን ለህዝቡ እያሰረጹ መሆኑን ገልጸዋል።

የቅስቀሳና ክርክር መርሐ ግብሮቹ ህዝቡ ለሀገር እድገት የተሻለ አማራጭ ሀሳብ የያዘ ፓርቲ በመለየት በምርጫ ጊዜ ሳይቸገር ለመምረጥ የሚያስችሉ መሆናቸውን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም