ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ፈጣን ልማት እንግዶቿን በውበትና ታሪካዊ መስህቦቿ የምታስደምም የቱሪስት መዳረሻ እያደረጋት ነው 

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 21/2018 (ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ ፈጣን የዕድገት ጉዞ መዲናዋ የታላላቅ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶች ማዕከል ብቻ ሳትሆን እንግዶቿን በውበትና ታሪካዊ መስህቦቿ የምታስደምም የቱሪስት መዳረሻም እያደረጋት መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ የቱሪዝም ኮሚሽን ገለጸ።

በኢትዮጵያ ሀገራዊ ለውጥ ማግስት አዲስ አበባን እንደስሟ ውብና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ከተማ ለማድረግ የተከናወኑ የልማት ሥራዎች ተጨባጭ ውጤትን አስገኝተዋል።

ለአብነትም በኮሪደር ልማት ከተማዋን ለሰው ልጅ ኑሮ ምቹ፣ ፅዱና ማራኪ በማድረግ ስሉጥ የእግረኛ፣ የብስክሌት፣ የመኪና መንገዶችን ጨምሮ አረንጓዴ መናፈሻ የልማት ሥራዎች ተገንብተዋል።

በቱሪዝም ዘርፍም የብሔራዊ ቤተ-መንግስት ዕድሳት፣ የዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ የገበታ ለሸገር ፕሮጀክቶችና የሳይንስ ሙዚየም የከተማዋን ገፅታ የቀየሩ ወሳኝ የልማት ስኬቶች ናቸው።

በመሠረተ ልማትና ከተማ ውበትም የህንፃዎች ዕድሳት፣ የመንገድ መብራቶችና የዲጂታል ማስታወቂያዎች የከተማዋን ውበት የበለጠ እያደመቁት ይገኛል።

የመዲናዋ ሁለንተናዊ የልማት ስኬትም የሀገር ውስጥና የዓለም አቀፍ የቱሪስት ፍሰትን በማሳደግ አዲስ አበባን የቱሪዝም ማዕከል እያደረጋት ነው።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር ሁንዴ ከበደ ለኢዜአ እንዳሉት፥ በአዲስ አበባ የተመዘገቡ ስኬታማ የለውጥ ሥራዎች መዲናዋን የመስህብ መዳረሻ እያደረጋት ነው።

በ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራትም የሀገር ውስጥና የዓለም አቀፍ ጎብኝዎች ፍሰት በማሳደግ ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ የቱሪስት ፍሰትም የቱሪዝም ዘርፍ በሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የሚጠበቅበትን አዎንታዊ ሚና የሚያበረክትበትን ወሳኝ ዕድል እየፈጠረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ይህም የዜጎችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት በማሳደግ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንዲሻሻል እያደረገ መሆኑን አንስተዋል።

በሌላ መልኩም የአዲስ አበባ አስደማሚ የለውጥ ሥራዎች መዲናዋን የአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የኮንፈረንስ ማዕከል መዳረሻ እያደረጋት እንደሚገኝ አስረድተዋል።

አዲስ አበባ የታላላቅ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶች ማዕከል ብቻ ሳትሆን እንግዶቿን በውበትና ታሪካዊ መስህቦቿ የምታስደምም የቱሪስት መዳረሻም ሆናለች ብለዋል።

በአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶች የሚሳተፉ እንግዶችም የመዲናዋን አስደማሚ ለውጥ በመጎብኘት የኢትዮጵያን ብሩህ ገፅታ ለዓለም በማስተዋወቅ የማይተካ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ለአብነትም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ ከ200 በላይ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ኩነቶችን በስኬት በማስተናገድ በኮንፈረንስ ቱሪዝም ልማት ከፍተኛ ስኬት መገኘቱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም