አዲስ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማግኘት የሚፈልጉ ደንበኞች በረጅም ጊዜ ክፍያ ተጠቃሚ የሚሆኑበት አሰራር ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማግኘት የሚፈልጉ ደንበኞች በረጅም ጊዜ ክፍያ ተጠቃሚ የሚሆኑበት አሰራር ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 21/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አዲስ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማግኘት የሚፈልጉ ደንበኞችን በረጅም ጊዜ ክፍያ ተጠቃሚ የሚያደርግ አሰራር ይፋ አድርጓል።
የአገልግሎቱ ማርኬቲንግ ሽያጭና ደንበኞች አገልግሎት ሥራ አስፈፃሚ ኢሳያስ ደንድር፤ የአገልግሎቱን አዲስ የክፍያና የአሰራር ሥርዓት በማስመልከት ለመገናኛ ብዙኅን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም፤ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የደንበኞችን አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት የሚያስጠብቅ ዘመናዊ የአሰራር ሥርዓቶችን ተግባራዊ እያደረገ ነው ብለዋል።
የህብረተሰቡን የአገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት ለማስፋትም የተከናወኑ ተግባራትም የደንበኞችን ቁጥር በመጨመር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።
አዲሱ የአገልግሎቱ አሰራርም የኤሌክትሪክ ኃይል ፈልገው በአንድ ጊዜ መክፈል ያልቻሉ ደንበኞች ተጠቃሚ የሚሆኑበት መሆኑን አስታውቀዋል።
ይህ የአሰራርም ያስፈለገው ማንኛውም አዲስ የኤሌክትሪክ ቆጣሪ የሚፈልግ ደንበኛ በገንዘብ ውስንነት ምክንያት ወደኋላ እንዳይቀር በማሰብ መሆኑን ተናግረዋል።
ለአዲስ ኃይል ማስቀጠያ የሚያስፈልገው ክፍያን የመክፈል አቅም መፍትሔ ለመስጠትም እስከ 24 ወራት (ሁለት ዓመት) የሚቆይ የጊዜ ገደብ ክፍያ ሥርዓት ተግባራዊ የሚያደረግ መሆኑን አስረድተዋል።
ደንበኞችም በየወሩ ከሚከፍሉት የአገልግሎት ክፍያ ጋር እየተደመረ የሚከፍሉበት አሰራር እንደሆነም ተናግረዋል።
የአሰራሩም ሙሉ ክፍያውን በአንድ ጊዜ መክፈል የማይችሉ ደንበኞች የመክፈል አቅም ችግር ያለባቸውን ደንበኞች እፎይታ ለመስጠት ያለመ ነው ብለዋል።
በአዲሱ አሰራር ላይ የጊዜ ገደብ ክፍያ ሥርዓት ተጠቃሚ ለመሆን ማመልከት፣ የማስገመቻ ሙሉ ክፍያ መክፈል፣ ከጠቅላላው የማስቀጠያ ክፍያ የተቀመጠውን ዝቅተኛ የቅድመ ክፍያ መጠን 10 በመቶ መክፈል፣ አመልካቹ የሚሰጠውን የጊዜ ገደብ በክፍያ በየወሩ ክፍያውን ለመፈጸም የውል ስምምነት መፈረም የሚችልና ውሉን ለማክበር ፈቃደኛ የሆነ እና መሰል መስፈርቶች ማካተታቸውን አስረድተዋል።
ይህ አሰራር ተግባራዊ የሚሆነው ለነጠላ ፌዝ (Single Phase) ቆጣሪ አመልካቾች ብቻ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡