ቀጥታ፡

ነዋሪዎች የምርጫ ካርድ ለመውሰድ ያሳዩት ከፍተኛ ተነሳሽነት ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያላቸውን ቁርጠኝነት ያስመሰከረ ነው 

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 21/2018 (ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የምርጫ ካርድ ለመውሰድ ያሳዩት ከፍተኛ ተነሳሽነት ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያላቸውን ቁርጠኝነት በተግባር ያስመሰከረ መሆኑን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ።

የአዲስ አበባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ መጠናቀቅን  አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥቷል።

መግለጫውን የሰጡት የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ማሩ ጃኔ፤ የጋራ ምክር ቤቱ በከተማዋ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙርያ ከከተማው አስተዳደር ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሂደትም ምክር ቤቱ የመዲናዋ ነዋሪዎች የመራጭነት ካርድ እንዲወስዱ በተለያየ መንገድ ግንዛቤ ሲያስጨብጥ መቆየቱን ተናግረዋል።

 ምርጫውን በተመለከተም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውጤታማ ውይይቶች መደረጋቸውን አንስተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የምርጫ ካርድ በማውጣት ያሳየው ከፍተኛ ተነሳሽነትና ቁርጠኝነትም ህብረተሰቡ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያለውን ፍላጎት በተግባር ያስመሰከረ መሆኑን ተናግረዋል።

የመራጮች ምዝገባ መጠናቀቅ የምርጫው መጀመሪያ እንጂ መጨረሻ አለመሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይ በሚከናወኑ ተግባራት ላይ ሁሉም አካላት በትኩረት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ምክር ቤቱም ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅ የሚጠበቅበትን ሚና እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።

የጋራ ምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ ዘሪሁን ኮርሜ በበኩላቸው፤ ምክር ቤቱ ምርጫው ፍትሐዊ፣ ነጻ እና ሰላማዊ እንዲሆን የሚጠበቅበትን ሚና እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ውይይቶችን በማድረግ የጋራ ተግባቦትን እየፈጠረ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅም ከምርጫ ቦርድ ጋር በቅንጅት  እየሰራ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

በተጨማሪም በምርጫው የህብረተሰቡ ንቃተ ህሊና እንዲዳብር የተደራጀ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም ምክር ቤቱ ለምርጫው ስኬታማነት ሚናውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም