በክልሉ ጥራትና ደህንነቱ የተረጋገጠ ከ169 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር እየተሰራጨ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ጥራትና ደህንነቱ የተረጋገጠ ከ169 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር እየተሰራጨ ነው
ባህርዳር ፤ ሚያዝያ 21/2018 (ኢዜአ)፦በአማራ ክልል ለ2018/19 የምርት ዘመን ጥራትና ደህንነቱ የተረጋገጠ ከ169 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ እየተሰራጨ መሆኑን የክልሉ የግብርና ጥራትና ደህንነት ባለስልጣን አስታወቀ።
የባለስልጣኑ ምክትል ኃላፊ አቶ ዘላለም ልየው ለኢዜአ እንደገለፁት፤ጥራትና ደህንነቱ በላብራቶሪ የተረጋገጠ ዘር ለአርሶ አደሩ ተደራሽ በማድረግ የክልሉን ምርታማነት ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው።
በዚህም ለ2018/2019 የምርት ዘመን ጥቅም ላይ የሚውል ከ169 ሺህ ኩንታል በላይ የበቆሎ፣ ስንዴ፣ ማሽላ፣ ጤፍና ሌሎች የሰብል ዘር ጥራትና ደህንነት በላብራቶሪ በማረጋገጥ እየተሰራጨ መሆኑን ገልጸዋል።
የዘር ጥራትና ቁጥጥር ስራው የተካሄደው በአማራ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ፣ በግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን፣ በዩኒየኖችና በግል ዘር አብዢዎች የቀረበውን መሆኑን ጠቅሰዋል።
የዘር ጥራትና ደህንነቱ በላብራቶሪ ተፈትሾና ተረጋግጦ በህብረት ስራ ማህበራትና በዘር አብዢዎች አማካኝነት ለአርሶ አደሩ የሚሰራጨው ምርጥ ዘርም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል።
አርሶ አደሩም ጥራትና ደህንነቱ የተረጋገጠ ዘር ገዝቶ በመጠቀም ምርታማነቱን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነቱን ለማረጋገጥ እንዲሰራ መክረዋል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ የዘር ብዜት ባለሙያ አቶ ጥላዬ ሞገሴ እንዳሉት ከባለስልጣኑ ጋር በመተባበር ለአርሶ አደሩ የሚቀርበውን ዘር ጥራት በማረጋገጥ ለገበያ የሚተርፍ ምርት ለማምረት እየተሰራ ነው።
በዚህም አርሶ አደሩ በህገወጥ መንገድ ዘርን ገዝቶ እንዳይጠቀም ተከታታይ ትምህርት በባለሙያዎች እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ በዘንድሮው የመኸር አዝመራ ከ5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች በዘር እንደሚሸፈን ከክልሉ ግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።