የኢትዮጵያን የፈጠራ ባለቤትነት መብት ጥበቃ ከዓለም አቀፍ መመዘኛዎች ጋር የሚያጣጥም የሕግ ማሻሻያ እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን የፈጠራ ባለቤትነት መብት ጥበቃ ከዓለም አቀፍ መመዘኛዎች ጋር የሚያጣጥም የሕግ ማሻሻያ እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 21/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያን የፈጠራ ንብረት ባለቤትነት መብት ጥበቃ ከአህጉራዊና ዓለም አቀፍ መመዘኛዎች ጋር የሚያጣጥም አዳዲስ የሕግ ማሻሻያ እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ገለጸ።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወልዱ ይመስል ለኢዜአ እንዳሉት፤ የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ የሚሹ ሃብቶች ሕጋዊ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ለሚጠይቁ ዜጎች አገልግሎት እየተሰጠ ነው።
የአዕምሯዊ ንብረት መብትና ባለቤትነት ጥበቃን ለማዘመንም ዘመናዊ የአሰራርና የሕግ ማዕቀፎችን በማዘጋጀት ተግባራዊ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
ለአብነትም ረጅም ዘመናትን ያስቆጠሩ ተቋማዊ ሕግጋትን በማሻሻል ዘመኑን የዋጀ የአሰራር ሥርዓት እንዲፈጠር መደረጉን አንስተዋል።
የአሰራርና የሕግ ማዕቀፎቹም የኢትዮጵያን የአዕምሯዊ ንብረት መብትና ባለቤትነት ጥበቃ ሊደረግላቸው የሚገቡ ሃብቶችን ማስጠበቅ እያስቻሉ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን የአዕምሯዊ ንብረት ባለቤትነት መብት ጥበቃ ከዓለም አቀፍ መመዘኛዎች ጋር የሚያጣጥም አዳዲስ የሕግ ማሻሻያ እየተደረገ እንደሚገኝም አስገንዝበዋል።
የባለስልጣኑ ዘመናዊ የአሰራርና የሕግ ማሻሻያም የአዕምሯዊ ንብረት መብትና ባለቤትነትን በማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በተጨማሪም የሙያተኞችን የመፈጸም አቅም በማጎልበት የአገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን የሚያረጋግጥ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዓመታት በፊት በተለያዩ ዘርፎች ይሰጥ የነበረውን ከ3ሺህ የማይበልጥ የአዕምሯዊ ንብረት መብትና ባለቤትነት ጥበቃ አሁን ላይ በዓመት ወደ 9ሺህ ምዝገባ ማድረግ የሚቻልበት አቅም መፈጠሩን ጠቅሰዋል።
በኢትዮ-አሊያንስ አድቮኬሲ የአዕምሯዊ ንብረትና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ደሱ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ የሕግ ማሻሻያዎች አሰራርን በማዘመን ገንቢ ሚና አላቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያን የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ውጤታማነትን ለማረጋገጥም የዓለም አቀፍ ተቋማትን ትብብር የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።
በቀጣይም የኢትዮጵያን የአዕምሯዊ ንብረት ሃብቶች ጥበቃ የበለጠ ለማጠናከር ሕግጋትን ማዘመንና የሙያተኞችን ብቃት ማጎልበት እንደሚገባ ተናግረዋል።