ቀጥታ፡

በሐረሪ ክልል በትምህርት ተሳትፎና ጥራት ላይ የተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት እያመጡ ነው

ሐረር ፤ ሚያዝያ 21/2018 (ኢዜአ)፦በሐረሪ ክልል የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋፋትና የትምህርት ጥራትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የተከናወኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

በትምህርት ስርዓቱ ውስጥ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በዘላቂነት ለመቅረፍ፣ መንግስት ከስርዓተ-ትምህርት ዝግጅት እስከ ግብዓት አቅርቦት ያሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በትኩረት እያከናወነ ይገኛል።

ጥራት ያለው ትምህርትን ለማረጋገጥ የቅድመ መደበኛ ትምህርትን መሠረት ከማጠናከር ጀምሮ፣ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል፣ የግብዓት አቅርቦትን ማሟላትና የመምህራን አቅም ግንባታ ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል።

የሐረሪ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ነገዎ እንደተናገሩት፤ በትምህርት ዘርፉ የሚስተዋሉ ስብራቶችን ለመጠገን የተከናወኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራት በክልሉ የትምህርት ጥራትና ተሳትፎ ላይ ተጨባጭ ለውጥ እያመጡ ነው።

በተለይም ህብረተሰቡን በማሳተፍ በክልሉ በሁሉም ከተማና ገጠር ቀበሌዎች ከቅድመ መደበኛ እስከ 8ኛ ክፍል ትምህርት ቤት በመገንባት ህጻናት ከቀያቸው ሳይርቁ ትምህርት እንዲያገኙ ከማድረግ ባለፈ የክልሉ የትምህርት ተሳትፎም 94 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል።

የትምህርት ጥራትን ከማረጋገጥ አንጻር ቢሮው ለትምህርት ቤት የሚያስፈልጉ  የትምህርት ግብዓቶችን የክልሉ መንግስት በመደበው በጀት  የማሟላት ስራ ሲያከናውን መቆየቱን ጠቅሰዋል።

ለትምህርት ጥራቱ መሻሻል ምክንያት የመምህራን ምዘና አንዱ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ጌቱ በዚህም በክልሉ  ዘንድሮ የመምህራን ምዘና ፈተና በበይነመረብ መሰጠቱን ተናግረዋል።

ለተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት የመስጠት፣ የትምህርት ምዕራፎችን በወቅቱ የመሸፈን፣ የምዘና ፈተናዎችን የመስጠትና ሌሎች ተግባራት በየትምህርት ቤቱ እየተከናወኑ መሆኑንም አንስተዋል።

በዚህም በክልሉ በሀገር አቀፍና በክልሉ የሚሰጡ የ12ኛ፣ 8ኛና 6ኛ ክፍል ፈተናዎች የተማሪ ውጤቶች በየዓመቱ መሻሻል እያሳየ እንደሚገኝ ጠቁመው በዘንድሮ ዓመትም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።


 

መንግስት ባስቀመጠው የትምህርት ተደራሽነትና ጥራት ላይ መሰረት ያደረጉ ተግባራት መከናወናቸውንና ውጤትም መገኘቱን  የተናገሩት ደግሞ በሐረር የጌይ መድረሳ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ኡስማኢል ኢብራሂም ናቸው።

በተለይም የተማሪዎችን ውጤት በማሻሻል አንጻር የትምህርት ግብዓት ከማሟላትና ከመማር ማስተማር ስራው ጋር በተያያዘ አበረታች ስራዎች መከናወኑንና የተሻለም ውጤት እንደሚጠብቁም አክለዋል።


 

በክልሉ የ6ኛ እና 8ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት፤ መምህራን የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠትና የፈተና ጥያቄዎችን በማሰራት እየረዷቸው መሆኑ የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ  ትልቅ እገዛ ያደርግላቸዋል።


 

በፈተናው ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ በትጋት እየተዘጋጁ መሆኑንም ተማሪዎቹ  ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም