ቀጥታ፡

በጅማ ዞን የመኸር ወቅት እርሻ ስራ ተጀምሯል

ጅማ ፤ ሚያዝያ 21/2018 (ኢዜአ)፦ በጅማ ዞን በመኸር ወቅት 883 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ ሰብሎች ለማልማት ታቅዶ የእርሻ ስራ መጀመሩን የዞኑ ግብርና ፅህፈት ቤት አስታወቀ።

የፅህፈት ቤቱ ሀላፊ አቶ ቲጃኒ ተማም ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ ግብርናውን በማስፋትና በማዘመን ምርትና ማርታማነትን ለማሳደግ በተሰጠ ትኩረት አበረታች ውጤት እየተገኘ ነው።


 

በተያዘው 2018/19 ምርት ዘመን በመኽር ወቅት 883 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ ሰብሎች በማልማት 36 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን ተናግረዋል።

እስካሁንም በምርት ወቅቱ ከሚለማው አጠቃላይ መሬት ውስጥ 13 በመቶ የሚሆነው ታርሶ ቀድመው በሚዘሩ በቆሎና ማሽላ ሰብሎች ዘር መሸፈኑን ጠቅሰዋል።

ለምርት ወቅቱ ለምርት ማሳደጊያ የሚያስፈልገው ግብአት በወቅቱ ለአርሶ አደሩ እየቀረበ መሆኑን ጠቁመው እስካሁንም ከ780 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ገብቶ ለአርሶ አደሩ እየተሰራጨ መሆኑን አመልክተዋል ።

በተጨማሪም 21 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር እየቀረበ መሆኑን ጠቁመው ግብአቱ ከወዲሁ መቅረቡ ወቅቱን የጠበቀ የዘር ስራ ለማካሄድ ማገዙን ተናግረዋል።

በቀጣይም የክረምቱን ዝናብ በመጠቀም ጤፍ እና ሩዝን ጨምሮ ሌሎችም የሰብል አይነቶች እንደሚዘሩ አመላክተዋል።


 

መንግስት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተገበራቸው ያለው የተለያዩ የግብርና ኢኒቬቲቮች ውጤት እያመጡ መሆናቸውን ጠቁመዋል።  

በዞኑ ከለውጡ በኋላ ግብርናውን ለማዘመን በ20 ወረዳዎች 1ሺህ 426 ትራክተሮች ለአርሶ አደሩ ቀርበው እየተሰራባቸው መሆኑንም አስታውቀዋል ።

በዞኑ ቀርሳ ወረዳ ነዋሪዎች አርሶ አደር ሙሀመድ አባቦር እና መሀመድ ኑር አባተማም በሰጡት አስተያየት አስፈላጊ የግብርና ግብቶችን ቀድመው በመውሰዳቸው መሬታቸውን በዘር መሸፈን ጀምረዋል።

በግብርና ባለሙያዎች ሙያዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ጠቁመው ከአምናው የተሻለ ምርት ለማግኘት አቅደው እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል ።

በዞኑ በመኽር ወቅት እርሻው ከ420 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች እንደሚሳተፉ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም