የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 29ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 29ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 21/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ዋንጫ ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ፣ ዛሬ በ29ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ወደ ውድድር ይመለሳል።
ከቀኑ 9 ሰዓት ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከመቻል በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ42 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል። መቻል በ44 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
በ28ኛ ሳምንት ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከኢትዮጵያ መድን ጋር አንድ አቻ ሲለያይ መቻል ከሃዋሳ ከተማ ያደረገው ጨዋታ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
ሁለቱም ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርጉት ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክር ይታይበታል።
በሌላኛው መርሐ ግብር ኢትዮጵያ መድን ከሃዋሳ ከተማ ከቀኑ 7 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ኢትዮጵያ መድን በ31 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። ሃዋሳ ከተማ በ43 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል።
የወቅቱ የሊጉ ሻምፒዮን ኢትዮጵያ መድን ባለፉት አራት ጨዋታዎች፣ ሀዋሳ ከተማ ደግሞ ባለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች አላሸነፉም።
ሁለቱም ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይፋለማሉ።
ከቀኑ 10 ሰዓት ሸገር ከተማ ከወላይታ ድቻ በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
ሸገር ከተማ በ35 ነጥብ ዘጠነኛ፣ ወላይታ ድቻ በ34 ነጥብ 11ኛ ደረጃን ይዘዋል።
በ28ኛ ሳምንት ሸገር ከተማ ባህር ዳር ከተማን 2 ለ 0፣ ወላይታ ድቻ ምድረ ገነት ሽሬን 1 ለ 0 አሸንፈዋል።
ሁለቱ ክለቦች ተከታታይ ድላቸውን ለማስመዝገብ ይጫወታሉ።
አዳማ ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ ምሽት 12 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
አዳማ ከተማ በ33 ነጥብ 14ኛ ደረጃን ይዟል። ድሬዳዋ ከተማ በ32 ነጥብ 16ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ባለፉት ስምንት ጨዋታዎች ከድል የራቀው አዳማ ከተማ ማሸነፍ ከወራጅ ቀጠና በመጠኑ የሚርቅበት ወሳኝ ሶስት ነጥብ ያስገኝለታል።
በሊጉ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች የተሸነፈው ድሬዳዋ ከተማ ወደ አሸናፊነት መንገድ ለመመለስ ይጫወታል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 29ኛ ሳምንት እስከ ሚያዚያ 23 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።
ሲዳማ ቡና በ54 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው።
አቤል ያለው ከሲዳማ ቡና በ14 ግቦች የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን እየመራ ይገኛል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ አዲስ ግደይ በ10 ጎሎች ይከተላል።