ቀጥታ፡

በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ሃዋሳ ከተማ ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ይጫወታሉ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 21/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 23ኛ ሳምንት ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ። 

ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ሃዋሳ ከተማ ከአርባምንጭ ከተማ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።

ሃዋሳ ከተማ በ43 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል። አርባምንጭ ከተማ በ10 ነጥብ የመጨረሻው 14ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ያላሸነፈው ሃዋሳ ከተማ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል። ሶስት ነጥብ በድጋሚ ወደ አራተኛ ደረጃ እንዲመለስ ያደርገዋል።


 

በሊጉ ካሸነፈ አራት ወራት ያስቆጠረው አርባምንጭ ከተማ ከተሸነፈ ወደ ከፍተኛ ሊግ ይወርዳል። 

ቡድኑ ከ15 ጨዋታዎች በኋላ ድልን ለማጣጣም ይጫወታል።

አዳማ ከተማ ከባህር ዳር ከተማ ከረፋዱ አምስት ላይ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ባለፉት አራት የሊግ ጨዋታዎች ከድል የራቀው አዳማ ከተማ በ21 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃን ይዟል።

ባህር ዳር ከተማ በ16 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በ22ኛ ሳምንት በሊጉ መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 3 ለ 0 ተሸንፏል።

ሁለቱም ቡድኖች ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም