ታሪካዊው ፍልሚያ፦ አትሌቲኮ ማድሪድ እና አርሰናል ለመጀመሪያ ጊዜ በቻምፒዮንስ ሊግ - ኢዜአ አማርኛ
ታሪካዊው ፍልሚያ፦ አትሌቲኮ ማድሪድ እና አርሰናል ለመጀመሪያ ጊዜ በቻምፒዮንስ ሊግ
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 21/2018 (ኢዜአ)፦ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ አትሌቲኮ ማድሪድ ከአርሰናል የመጀመሪያ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታቸውን ዛሬ ያደርጋሉ።
የሁለቱ ክለቦች ጨዋታው ምሽት አራት ሰዓት ላይ በዋንዳ ሜትሮፖሊታኖ ስታዲየም ይካሄዳል።
በሩብ ፍጻሜው አትሌቲኮ ማድሪድ ባርሴሎናን በመርታት ለግማሽ ፍጻሜው አልፏል።
ተጋጣሚው አርሰናል ስፖርቲንግ ሊዝበንን በድምር ውጤት በማሸነፍ አራት ውስጥ ገብቷል።
ሁለቱ ክለቦች በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ሲገናኙ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ከዚህ ቀደም በአውሮፓ መድረክ የነበራቸው ግንኙነት ከሰባት ዓመት በፊት በዩሮፓ ሊግ ላይ ነው።
እ.አ.አ በ2018 በዩሮፓ ሊግ በግማሽ ፍጻሜው ተገናኝተው አትሌቲኮ ማድሪድ በድምር ውጤት 2 ለ 1 በማሸነፍ ለፍፃሜ አልፏል።
ቡድኖቹ በመጀመሪያው የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ አንድ አቻ ሲለያዩ በመልሱ ጨዋታ አትሌቲኮ ማድሪድ 1 ለ 0 አሸንፏል።
አትሌቲኮ ማድሪድ በወቅቱ በፍጻሜው ማርሴይን 3 ለ 0 በማሸነፍ ዋንጫውን ማንሳቱ አይዘነጋም።
ሁለቱ ክለቦች ከሰባት ዓመታት በኋላ በታላቁ መድረክ ለመጀመሪያ ጊዜ ይጫወታሉ።
አትሌቲኮ ማድሪድ እና አርሰናል የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን አንስተው አያውቁም።
የማድሪዱ ክለብ በሻምፒዮንስ ሊጉ ሶስት ጊዜ ለፍጻሜ ደርሶ ተሸንፏል።
አርሰናል እ.አ.አ በ2005/06 የውድድር ዓመት ለፍጻሜ ደርሶ በባርሴሎና 2 ለ 1 ተሸንፎ ዋንጫውን አጥቷል።
ሁለቱም ቡድኖች እስካሁን የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን አለማንሳታቸው፣ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታውን በጉጉት እንዲጠበቅ ያደርገዋል።
ቡድኖቹ ያንን የታሪክ ክፍተት ለመሙላት ከፍተኛ ጥማት አላቸው።
ሁለቱ ክለቦች በዘንድሮው ሻምፒዮንስ ሊግ በሊግ እርከን (League Phase) ተገናኝተው አርሰናል 4 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።