ቀጣናዊ የሽምግልና ጥረቶች በጠንካራ ፖለቲካዊ መሰረት ላይ ሊገነቡ ይገባል - ኢጋድ - ኢዜአ አማርኛ
ቀጣናዊ የሽምግልና ጥረቶች በጠንካራ ፖለቲካዊ መሰረት ላይ ሊገነቡ ይገባል - ኢጋድ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 20/2018 (ኢዜአ)፦ በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሚደረጉ የሽምግልና ጥረቶች በጠንካራ ፖለቲካዊ መሰረት ላይ ሊገነቡ ይገባል ሲሉ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ዋና ጸሀፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ገለጹ።
የመጀመሪያው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የሽምግልና ምክክር ጉባኤ ዛሬ በኬንያ ናይሮቢ መካሄድ ጀምሯል።
ጉባኤው እየተካሄደ የሚገኘው “ሽምግልናን በተከፋፈለ ዓለም ውስጥ በአዲስ መልክ መቃኘት፦ የአፍሪካ ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ፈተናዎች” በሚል መሪ ሀሳብ ነው።
የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)፣ የኬንያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሙሳሊያ ሙዳቪዲ እና አጋር አካላት በጉባኤው ላይ ተገኝተዋል።
ውይይቱ በፍጥነት እየተቀያየረ ባለው ዓለም አቀፋዊ ሥርዓት ውስጥ የሽምግልና የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ያተኮረ ነው።
የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ለኢጋድ ሽምግልና እንደ አማራጭ የሚታይ የዲፕሎማሲ ዘርፍ ሳይሆን፣ ተቋሙ በዋነኛነት ሊወጣው የሚገባው ቀዳሚ የፖለቲካ ግዴታ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል።
የሽምግልና ጥረቶች ፍሬ ማፍራት ወይም አለማፍራት፣ ተቋሙ ያለውን የጋራ አመራር ብቃትና ተቋማዊ ክብደት የሚፈትን ትልቅ አጋጣሚ ነው ብለዋል።
በአፍሪካ ቀንድ የሚደረጉ የሽምግልና ጥረቶች ስኬታማ እንዲሆኑ ከተበታተነ አካሄድ ወጥተው፣ በአንድ ወጥ ስትራቴጂያዊ መሪ ዕቅድ የሚመሩና የጠነከረ ፖለቲካዊ መሰረት ያላቸው ሊሆኑ እንደሚገባም አንስተዋል።
ማንኛውም የዲፕሎማሲ ድርድር በግጭት ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ህይወትና ደህንነት ዋና ማዕከሉ ሊያደርግ ይገባልም ነው ያሉት።
በፍጥነት እየተቀየረ ካለው የዓለም ስርዓት አኳያ ሽምግልናን በአዲስ መልክ መቃኘት እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።
የመጀመሪያው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የሽምግልና ምክክር ጉባኤ እስከ ነገ እንደሚቆይ ኢዜአ ከኢጋድ ሴክሬታሪያት ያገኘው መረጃ ያመለክታል።