ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በለውጡ ዓመታት በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ሰፊ ሥርዓታዊ ሽግግር አድርጋለች  

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 20/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ባለፉት ስምንት የለውጥ ዓመታት በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ሰፊ ሥርዓታዊ ሽግግር ማድረጓን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

‘‘የማህበራዊ ልማት እመርታ ለሀገር ግንባታ’’ በሚል መሪ ቃል፣ በማህበራዊ ዘርፍ ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡ ዐበይት ውጤቶች የቀረቡበት የምክክር መድረክ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተካሂዷል።

በዚህም ባለፉት ዓመታት በማህበራዊ ዘርፎች የተመዘገቡ ወሳኝ ስኬቶች መቅረባቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

በስምንት የለውጥ ዓመታት ኢትዮጵያ በመሰረታዊና ማህበራዊ ዘርፎች የተስተዋሉ ክፍተቶች ላይ ትኩረት በማድረግ፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ሰፊ ሥርዓታዊ ሽግግር ማድረጓን አመልክቷል።


 

በትምህርት ዘርፍ አዲስ ሥርዓተ-ትምህርትን በመተግበር፣ የመማሪያ መጽሐፍት ስርጭትን በማሻሻል እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርትና የሀገር አቀፍ ፈተና ሥርዓቶችን በማዘመን፣ የትምህርት ዘርፉ ጥራትና ተዓማኒነት እንዲላበስ መደረጉን ተነስቷል።

በተመሳሳይ የጤናው ዘርፍ ለ30 ዓመታት የቆየውን ፖሊሲ በመከለስ፤ ከመከላከል ጎን ለጎን አክሞ የማዳን አገልግሎት ላይ ትኩረት መደረጉንና በዲጂታል ጤና፣ በሀገር ውስጥ የፋይናንስ ምንጭና በጤና ዲፕሎማሲ ረገድ ጉልህ ውጤቶች ተመዝግበዋል ብሏል።

የኢኮኖሚና ማህበራዊ አቅምን የመገንባት ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን የገለጸው ጽሕፈት ቤቱ፤ የሥራና ክህሎት ዘርፉ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠናን (TVET) በማዘመንና የቢዝነስ ማጠናከሪያ ማዕከላትን በማስፋፋት፣ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ከ19 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን አስታውቋል።

ይህ አካታችነትን ባማከለ ስኬት በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ዘርፍም የተደገመ ሲሆን፣ 26 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሴቶችንና 4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ወጣቶችን በኢኮኖሚ እና በፖለቲካ ተሳትፎ ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ ለተጋላጭ ዜጎችና በአደጋ ለተጎዱ ወገኖች የተሻለ ጥበቃ እንዲደረግ ማስቻሉን ገልጿል።


 

በባህልና ስፖርት ዘርፉም የሀገሪቱን ቅርሶች ለብሔራዊ አንድነትና ለዲፕሎማሲ ስኬት እንዲውሉ በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና መጫወቱን አመልክቷል።

ከእነዚህም መካከል 83 የአደባባይ ክብረ በዓላት እውቅና ማግኘታቸው፣ 36 የባህል ማዕከላት መገንባታቸው እንዲሁም አደይ አበባ ስታዲየምን ጨምሮ ከመቶ ሺህ በላይ አዳዲስ የስፖርት መሠረተ ልማቶች መገንባታቸው የዘርፉ ጉልህ ስኬቶች መሆናቸውን ተመልክቷል።

በአጠቃላይ በዘርፎቹ የተመዘገቡ ለውጦች መንግሥት ለተቋም ግንባታ፣ ለዲጂታል ሽግግርና ለሰው ሀብት ልማት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳዩ መሆናቸውን ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም