ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በሚገጥሟት ተግዳሮቶች ሳትገደብ ከሚገመተው በላይ በከፍተኛ ፍጥነት እየተገነባች ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) 

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 20/2018 (ኢዜአ)፦  ኢትዮጵያ በሚገጥሟት ተግዳሮቶች ሳትገደብ ከሚገመተው በላይ በከፍተኛ ፍጥነት እየተገነባች እንደምትገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ። 

"የማህበራዊ ልማት እመርታ ለሀገር ግንባታ" በሚል መሪ ቃል፣ ባለፉት ዓመታት በማህበራዊ ዘርፍ የተመዘገቡ ዐበይት ውጤቶች የቀረቡበት የምክክር መድረክ ተካሄዷል። 


 

በዚሁ መድረክ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የልማት ስራዎቹን አስፈላጊነት በተመለከተ ሃሳባቸውን አጋርተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ዘርፍ የሚከናወኑ የግንባታ ስራዎች እንደ ሌሎች መሠረተ-ልማቶች ውጤታቸው ወዲያው የሚታይና የሚጨበጥ ባይሆንም፣ ለሀገር ዘላቂና ወሳኝ መሰረት የሚጥሉ መሆናቸውን በመልዕክታቸው ላይ ገልጸዋል። 

ኢትዮጵያ በሚገጥሟት ተግዳሮቶች ሳትገደብ ከሚገመተው በላይ በከፍተኛ ፍጥነት እየተገነባች መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ምንም እንኳን የዐቅም ውስንነቶች ቢኖሩም ለማሻሻል ያልተሞከረ የማህበራዊ ዘርፍ እንደሌለ አስገንዝበዋል።


 

በዘርፎቹ የታለመው ሁሉ በተግባር እንዲተረጎምና ተገቢውን ዓላማቸውን እንዲያሳኩ ገና ብዙ ሥራ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል። 

አንድ እጅ ብቻውን ማጨብጨብ እንደማይችል ሁሉ፣ መንግሥት የሚጀምራቸውን ሥራዎች ሌላው የማህበረሰብ ክፍል እንደ አንድ ባለ ድርሻ ኃላፊነት ወስዶ በጋራ መቆም እንደሚገባው አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም