ቀጥታ፡

ዜጎች በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ሊጠቀሙ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 20/2018(ኢዜአ)፦ዜጎች በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የመምረጥ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን መጠቀም እንደሚጠበቅባቸው የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ገለጹ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዘንድሮውን ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ከየካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሚያዝያ 14 ቀን 2018 ዓ.ም ሲያካሄድ ቆይቶ ተጠናቋል።

በቦርዱ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ድምፅ በሚሰጥበት ሲሆን በዲጂታል "ምርጫዬ" መተግበሪያና በየምርጫ ጣቢያዎቹ የተመዘገቡ መራጮች በአካል በመገኘት ድምፅ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው መረጃ ከ50 ሚሊዮን 514 ሺህ በላይ መራጮች ድምፅ መስጠት የሚያስችላቸውን የምርጫ ካርድ ወስደዋል። 

በተጨማሪም ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች፣ በዩኒቨርሲቲ ለሚገኙ ተማሪዎችና በካምፕ ለሚገኙ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት በልዩ ሁኔታ እስከ ሚያዝያ 24 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ በመመዝገብ የምርጫ ካርዳቸውን መውሰድ ይችላሉ።

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫም 47 ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች 10 ሺህ 934 ዕጩዎችን በማስመዝገብ በመገናኛ ብዙኅን አማካኝነት የፖሊሲ አማራጭ ሃሳባቸውን ለህዝብ በማስተዋወቅ ላይ ናቸው።

የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን፤ ምርጫ ዜጎች ዴሞክራሲያዊና ሕገ-መንግሥታዊ መብታቸውን የሚጠቀሙበት የአደባባይ መድረክ ነው ብለዋል።

ለዚህም ዜጎች በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስክ ልማትና ዕድገትን የሚያፋጥን ጠንካራ መንግስት ለመመስረት በምርጫ ሂደት የነቃ ተሳትፎ የማድረግ ሀገራዊ ግዴታ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የምርጫ ሂደትም በሃሳብ የበላይነት የተመሰረተ ጠንካራ መንግሥት ለመመስረት ዜጎች ይበጀኛል ለሚሉት የፖለቲካ ፓርቲ ድምፅ የሚሰጡበት የጋራ መድረክ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በግንቦት 2018 ዓ.ም ለምታካሂደው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነጻ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሕዊነትም የዜጎች የነቃ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም ዜጎች የወሰዱትን የምርጫ ካርድ በመጠቀም ይበጀኛል ለሚሉት የፖለቲካ ፓርቲ ድምፅ በመስጠት ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ለመጠቀም መዘጋጀት እንዳለባቸው አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም