የመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለትን ለማዘመን የተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች የሀገር ውስጥ ምርትን በማሳደግ ረገድ ተጨባጭ ስኬት እያስመዘገቡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለትን ለማዘመን የተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች የሀገር ውስጥ ምርትን በማሳደግ ረገድ ተጨባጭ ስኬት እያስመዘገቡ ነው
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 20/2018(ኢዜአ)፦የመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለትን ለማዘመን የተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች፤ የሀገር ውስጥ ምርትን በማሳደግ ረገድ ተጨባጭ ስኬት እያስመዘገቡ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ።
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት “ዓለም አቀፍ ስልታዊ አጋርነት ለአስተማማኝ የመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለት“ በሚል መሪ ሐሳብ ያዘጋጀው 5ኛው ዓለም አቀፍ የአቅራቢዎች ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ እንደገለጹት፤ የመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለትን ለማዘመን የተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች የኢትዮጵያን የጤና ኢንቨስትመንት ተወዳዳሪ ከማድረጋቸውም በላይ፣ የውጭ ምርትን በሀገር ውስጥ ለመተካት ለሚደረገው ጥረት ትልቅ ስኬት እያስመዘገቡ ይገኛሉ።
በተለይም ኢትዮጵያ ታምርት በተሰኘው ብሔራዊ ንቅናቄ አማካኝነት የሀገር ውስጥ መድኃኒት አምራቾች ተጨባጭ ድጋፍ እያገኙ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት አሥርተ ዓመታት ስትከተለው የነበረውን የጤና ፖሊሲ በመለወጥ፣ ከበሽታ መከላከል ባለፈ ለአክሞ ማዳን አገልግሎት ከፍተኛ ትኩረት መስጠቷን አስረድተዋል።
የመድኃኒት አቅርቦት ሥርዓቱን ለማዘመንም ዘመናዊ የማከማቻና ማከፋፈያ ማዕከላት በዲጂታል መረጃ መረብ እንዲገናኙ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተመረቀው አዲሱ የላቦራቶሪ ተቋም የሀገር ውስጥ ምርቶች ጥራታቸውን የጠበቁ እንዲሆኑና ለምርምር አመቺ ሁኔታን በመፍጠር ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለጎረቤት አገራትና ለአፍሪካ ቀንድ መድኃኒቶችን የማከፋፈል ራዕይ እንዳላት የገለጹት ሚኒስትሯ፤ የውጭ ባለሃብቶች በዘርፉ እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ በበኩላቸው፤ ቀልጣፋና አስተማማኝ የመድኃኒት አቅርቦት እንዲኖር የግዥ ሥርዓቱ በኤሌክትሮኒክስ እንዲደገፍና አጠቃላይ የአቅርቦት ሰንሰለቱ ዲጂታላይዝ መደረጉን ገልጸዋል።
የኮንፈረንሱ ዋና ዓላማም ከአቅራቢዎች ጋር ያለውን ግንኙነት በማጠናከር ሂደቱን ቀጣይነት ባለው መልኩ ለማሳለጥ መሆኑን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ መድኃኒት አምራቾች ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ታደሰ ተፈሪ፤ መድረኩ የሀገር ውስጥ አምራቾች ከዓለም አቀፍ አቅራቢዎች ልምድና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲያገኙ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
ማኅበሩም የሀገር ውስጥ አምራቾችን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ እየሠራ መሆኑንም ተናግረዋል።
ከተለያዩ ሀገራት የመጡ የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ያለውን እምቅ አቅም መመልከታቸውንና በቀጣይም ኢንቨስት ለማድረግ መነቃቃት እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል።
ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን የአቅርቦትና የአጋርነት ሥራ ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግሩትም አረጋግጠዋል።