ቀጥታ፡

መንግስት ለማዕድን ዘርፍ የሰጠው ትኩረት ተጨባጭ ውጤቶችን እያመጣ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ 

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 20/2018 (ኢዜአ)፦ መንግስት ለማዕድን ዘርፍ የሰጠው ትኩረት ተጨባጭ ውጤቶችን እያመጣ እንደሚገኝ ምክትል ጠቅላይ ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ የማዕድን ሀብት በማልማትና ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት በማዋል ረገድ ወደ ተጨባጭ ተግባር መሸጋገሯን አመልክተዋል።


 

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግራናይት የሚያመርተውን የኦርላመንት (3ኤም) ማርብልና ቴራዞ ማኑፋክቸሪንግ የሥራ እንቅስቃሴ መመልከታቸውን ጠቁመዋል።

ፋብሪካው በክልሉ የሚገኘውን ባለ ብዙ ቀለም የግራናይት ማዕድን በመጠቀም ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ምርት ለገበያ እያቀረበ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ለአካባቢው ማህበረሰብም የሥራ ዕድል ከመፍጠሩ ባሻገር የሀገር ውስጥ ፍላጎትን በመሸፈን የውጭ ምንዛሬን እንደሚያድንም ነው ያብራሩት።


 

መንግሥት የግሉ ዘርፍ በማዕድን ልማት ላይ በስፋት እንዲሳተፍ የፈጠረው ምቹ ሁኔታ፣ ማበረታቻና ድጋፍ ዛሬ ላይ እንዲህ ያሉ ተጨባጭ ውጤቶችን እያመጣ ነው ብለዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከወርቅ እስከ ግራናይት በተፈጥሮ የታደለ መሆኑን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህንን ፀጋ ለሀገር ብልጽግና ለማዋል የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ይበልጥ እንዲጠናከሩ የፌደራል መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም