ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራና በታዳሽ ኃይል ያስመዘገበችው ስኬት፤ የአየር ንብረት ጥበቃና ዘላቂ ዕድገት የማይነጣጠሉ መሆናቸውን በተግባር ያረጋገጠ ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 20/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራና በታዳሽ ኃይል ልማት የአየር ንብረት ለውጥ እና ዘላቂ ዕድገት የማይነጣጠሉ ቋሚ አጀንዳዎች መሆናቸውን በተግባር አሳይታለች ሲሉ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ክላቨር ጋቴቴ ገለጹ፡፡

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ከአፍሪካ ሕብረት፣ ከአፍሪካ ልማት ባንክና ሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር "የአጀንዳ 2030 እና 2063 ግቦችን ለማሳካት የተቀናጀና አሻጋሪ አካሄድ መከተል" በሚል መሪ ሐሳብ ያዘጋጀው 12ኛው የአፍሪካ ዘላቂ ልማት ቀጣናዊ ጉባኤ በአዲስ አበባ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መካሄድ ጀምሯል።


 

በየዓመቱ የሚካሄደው የአፍሪካ ዘላቂ ልማት ቀጣናዊ ጉባኤ የአፍሪካ ሕብረትን የአጀንዳ 2030 እና 2063 የዘላቂ የልማት ግቦችን አፈፃፀም ለመገምገም ነው። 

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ክላቨር ጋቴቴ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ እና በኢ-ተገማች የዓለም ነባራዊ ሁኔታ ተስፋና ሥጋት እያስተናገደች ነው። 

በአፍሪካ ቀጣይነት ያለው፣ አካታችና ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ ለመገንባት አህጉራዊ ለውጥና ሽግግር ያስፈልጋል ብለዋል። 

ኢነርጂ፣ መሠረተ ልማት ማስፋፋት፣ ከተማ ከማዘመን ባለፈ በሀገራት መካከል የእሴት ትስስር መፍጠር እንደሚገባ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን መቋቋም የሚያስችል ጠንካራ እርምጃ እየወሰደች መሆኑን በመግለፅ፤ ለአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ 2063 ግብ መሳካት ገንቢ ሚና አለው ብለዋል። 

ኢትዮጵያ የደን ሽፋኗን ለማሳደግ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን መትከሏን አስታውሰው፤ በዓለም የደን ልማት ዘርፍ ከፍተኛው ኢኒሼቲቭ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ 95 በመቶ ኃይል ከታዳሽ ኃይል የሚገኝ መሆኑን ገልጸው፤ ይህ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ወሳኝነት አለው ብለዋል። 

በአረንጓዴ አሻራ፣ በታዳሽ ኃይልና ከተማ ልማት የተመዘገቡ ስኬቶች ከኢትዮጵያ አልፎ ለሌሎች ሀገራት ዘላቂ ዕድገት ገንቢ ሚና እንደሚኖረውም ገልጸዋል። 

ኢኒሼቲቮቹ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን በመቋቋም የውኃ ደህንነትን ማረጋገጥ፣ መሰረተ ልማትን ማስፋፋት ያስችላሉ ብለዋል።

አፍሪካ የአጀንዳ 2030 እና 2063 ዘላቂ ግቦችን ለመፈጸም በምታደርገው ጥረት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡


 

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሉክ ባሃዱር ታፓ፤ በመላው አህጉሪቱ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም በሚያስችሉ ተግባራት፣ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ፣ በዲጂታል ሽግግርና በቀጣናዊ ትስስር ላይ ቁልፍ አመራር መስጠትና ዕውቀትን ማፍሰስ እንደሚገባ አመላክተዋል። 

ይህ የአህጉሪቱ አቅም ውጤታማ እንዲሆን ሰፊ ኢንቨስትመንት እንደሚፈልግ የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ በተለይም በጤና፣ በትምህርትና በዲጂታል ልማት ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ዘላቂ ልማት ያለ እኩልነትና ፍትሐዊ የፋይናንስ ሥርዓት ውጤታማ ሊሆን እንደማይችል በማንሳት፤ ቀጣይነት ያለው የአየር ንብረት ፋይናንስ ሥርዓት በመዘርጋት ተጎጂዎችን መድረስ እንደሚገባም ገልጸዋል። 

ለዚህም አባል ሀገራት የውስጥ ሀብት አሰባሰብን ማሳደግ፣ የግሉን ዘርፍ ማበረታታትና ከአጋር አካላት ጋር በትብብር መሥራት እንዳለባቸው ፕሬዝዳንት ሉክ ባሃዱር ታፓ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም