ቀጥታ፡

ከለውጡ በፊት የትምህርቱ ዘርፍ በእጅጉ የተጎዳ፣ ሰፊ እና አፋጣኝ ተሀድሶ ከሚያስፈልጋቸው ዘርፎች አንዱ ነበር-ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ 

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 20/2018 (ኢዜአ)፦ ከለውጡ በፊት የትምህርቱ ዘርፍ በእጅጉ የተጎዳ፣ ሰፊ እና አፋጣኝ ተሀድሶ ከሚያስፈልጋቸው ዘርፎች አንዱ ነበር ሲሉ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ።

‘’የማህበራዊ ልማት እመርታ ለሀገር ግንባታ’’ በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው እና በማህበራዊ ዘርፍ ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡ ዐበይት ውጤቶች የሚቀርቡበት የምክክር መድረክ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት እየተካሄደ ይገኛል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ባለፉት ስምንት የለውጥ ዓመታት በትምህርት ዘርፍ የተመዘገቡ ዓበይት ስኬቶችን አቅርበዋል።

‎ከለውጡ በፊት የትምህርቱ ዘርፍ በእጅጉ የተጎዳ፣ ሰፊ እና አፋጣኝ ተሀድሶ ከሚያስፈልጋቸው ዘርፎች አንዱ ነበር ያሉት ሚኒስትሩ፤ ዘርፉን በእጅጉ ተጭነውት የነበሩ ችግሮችን አንስተዋል።

ከችግሮቹ መካከል፤ የመሠረተ ልማት ጥራትና የግብዓት እጥረት፣ የተማሪ-መምህር፣ የተማሪ-ክፍል ጥመርታ አለመመጣጠን፣ ለትምህርት ዓይነቶች ብቁ የሆኑ መምህራን አለመኖር፣ የስርዓተ ትምህርት አግባብነትና የመጻህፍት ተደራሽነት ችግሮች፣ ኢ-ፍትሃዊነትና ኢ-እኩልነት፣ የትምህርት ሴክተሩ ትክክለኛነት መዳከም፣ ዝቅተኛ የቅድመ መደበኛ ትምህርት መኖር ከብዙ ማነቆዎች ጥቂቶች ነበሩ ብለዋል።

‎በዚህም በጥናት በተደገፈ መልኩ፤ የትምህርት ዘርፉን ፍላጎቶች እና ተግዳሮቶች በመለየት ከተመዘገቡ ዋና ዋና ለውጦች መካከል አቅርበዋል።

በዚህም የሥርዓተ-ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ፣ የመፅሃፍት ህትመት ስርጭትና ተደራሽነት፣ የመምህራንና የትምህርት አመራር ልማት የቅድመ መደበኛ ትምህርትን ማሳደግ፣ የትምህርት ቤት ደረጃ ማሻሻል፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሪፎርም፣ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን እና ዲጂታል ትምህርት መስፋፋት፣ የሀገር አቀፍ ፈተናዎች ዝግጅትና አስተዳደር መሻሻል፣ የትምህርትና ስልጠና ጥራት ማደግ ዋነኞቹ በለውጡ ተግባራዊ የሆኑና ውጤት ያስገኙ ሆነው መመዝገባቸውን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም