ቀጥታ፡

በለውጡ ዓመታት በጤና ዲፕሎማሲ ከፍተኛ እምርታ ተመዝግቧል -ዶክተር መቅደስ ዳባ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 20/2018 (ኢዜአ)፦ ባለፉት ስምንት የለውጥ ዓመታት በጤና ዲፕሎማሲ ዘርፍ ከፍ ያሉ እምርታዎች መመዝገባቸውን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ።

"የማህበራዊ ልማት እመርታ ለሀገር ግንባታ" በሚል መሪ ቃል በማህበራዊ ዘርፍ ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡ ዓበይት ውጤቶች የሚቀርቡበት የምክክር መድረክ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት እየተካሄደ ይገኛል።

በመድረኩ ላይ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ ባለፉት ስምንት የለውጥ ዓመታት በጤና ዘርፍ የተመዘገቡ ዓበይት ስኬቶችን ያቀረቡ ሲሆን፤ ዘርፉ ከለውጡ በፊት የነበሩ ክፍተቶችን በመለየት ያስመዘገባቸውን ዋና ዋና ውጤቶች ዘርዝረዋል።

ለ30 ዓመታት የቆየውን የጤና ፖሊሲ በመከለስ፣ ከመከላከል መርህ በተጨማሪ አክሞ የማዳን ቁርጠኛ የፖሊሲ አመራር፣ የተቋም ግንባታ እና የጤና መሠረተ ልማት ለውጦች መከናወናቸውን ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

በተጨማሪም የመድሃኒት፣ የክትባት እና የህክምና ግብዓቶች ምርት አቅርቦት እና ቁጥጥር መጨመሩን እንዲሁም የጤና ፋይናንስ እመርታ መመዝገቡን የለውጡ ቁልፍ እና ዋና ስራዎች አድርገው አቅርበዋል።

በተለይም የወረርሽኝ ልየታ እና ቁጥጥር፣ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና እንክብካቤ፣ የጤና ባለሙያዎችን ማብቃትና ቁጥራቸውን ማሳደግ፣ የዲጂታል ጤና እና በዘርፉ የተተገበሩ ልዩ ልዩ የበጎ አድራጎት ስራዎች ኢትዮጵያ በጤና ዘርፍ ያስመዘገበቻቸው ግንባር ቀደም ስኬቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የጤና ዲፕሎማሲ ዘርፍ ከፍተኛ እመርታ የታየበት መስክ መሆኑን የገለጹት ዶክተር መቅደስ፤ ይህም ኢትዮጵያ በተለያዩ መድረኮች ከአፍሪካ በቀዳሚነት ተመርጣ ድርድሮችን እና ንግግሮችን እንድትመራ ማስቻሉን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም