ቀጥታ፡

ከስልጠናው ያገኘነው እውቀት ወቅቱ የሚጠይቀውን ብቁ ማህበራትን ለመፍጠር ያግዘናል-ሰልጣኞች

አሶሳ፤ ሚያዝያ 20/2018(ኢዜአ)፦ ከስልጠናው ያገኘነው እውቀት ወቅቱ የሚጠይቀውን ብቁ የህብረት ስራ ማህበራትን ለመፍጠር ያግዘናል ሲሉ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የህብረት ስራ ማህበራት አመቻች ባለሙያዎች ተናገሩ።

በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ "ወደ ቀበሌ መድረስ " በሚል መሪ ሃሳብ ለህብረት ስራ ማህበራት አመቻች ባለሙያዎች ላለፉት ስምንት ቀናት  ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቋል።

የስልጠናው ተሳታፊዎች በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ስልጠናው ህብረት ስራ ማህበራት ላይ እየተስተዋለ ያለውን የአደረጃጀት ችግር በመቅረፍ በአዲስ መልክ ወደ ስራ እንዲገቡ የሚያደርግ ነው።

ከሰልጣኞቱ መካከል አቶ አምሳሉ ቀነኒ፤ ስልጠናውን ከፍተኛ ልምድ ባላቸው የዘርፉ ባለሙያዎች መውሰዳቸው ዘርፉን ለመለወጥ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ነው የገለጹት።


 

በህብረት ስራ ማህበራት ላይ የሚታዩ የአደረጃጀት እና የፋይናንስ አቅርቦት ችግሮችን በማስተካከል ጠንካራ እና ራሳቸውን የሚያስተዳድሩ ማህበራትን ለመፍጠር እንደሚረዳም እንዲሁ።

በተጨማሪም ማሕበራቱን በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ በተሻለ መንገድ በቀጥታ ተሳታፊ ለማድረግም ሰፊ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ነው የተናገሩት።

በወሰዱት ስልጠና መሠረትም  የህብረት ስራ ማህበራቱ በአዲሱ ሪፎርም መሠረት ወደ ስራ እንዲገቡ ለማድረግና አዳዲስ አሰራሮችን ለመተግበር እንደሚሰሩም ነው ያረጋገጡት።


 

ስልጠናው መሠረታዊ የህብረት ስራ ማህበራትን አሁናዊ ቁመና ከመዳሰስ ባለፈ ኢኮኖሚውን ከማረጋጋት አንፃር ያለውን  ክፍተት አሳይቶናል ያሉት ደግሞ  ሰልጣኝ አዚዛ አደም ናቸው።

የሂሳብ አያያዝ፣ አደረጃጀት እንዲሁም የድጋፍ እና ክትትል ስራዎችን የበለጠ በማጠናከር የህብረት ስራ ማህበራት ሪፎርሙን እንዲተገብሩ የሚያደርግ በመሆኑም ለስኬታማነቱ እንሰራለን ብለዋል።

ስልጠናው የህብረት ስራ ማህበራትን አደረጃጀትን በማዘመን እና ከነበሩበት የቆየ  አሰራር በማላቀቅ ወቅቱ የሚጠይቀውን ብቁ ማህበራትን ለመፍጠር ያግዛል ያሉት ደግሞ ማሊክ ዩሱፍ ናቸው።


 

የህብረት ስራ ማህበራት ለህብረተሰቡ ቅርብ በመሆናቸው መሠረታዊ አገልግሎቶችን ተደራሽ በማድረግ ተልዕኳቸውን እንዲወጡ እንሰራለን ነው ያሉት።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መሬትና ህብረት ስራ ማደራጃ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኑረዲን ሙክታር በበኩላቸው፤ ሪፎርሙ የህብረት ስራ ማህበራት ብቁ የሰው ሀይል በመያዝ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ እንዲሆኑ የሚያደረግ ነው ብለዋል።


 

በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ያለው ይህ የህብረት ስራ ማህበራት ንቅናቄ ውጤታማ እንዲሆን አመቻች ባለሙያዎች ያገኙትን ስልጠና በመተግበር ተጨባጭ ለውጥ ማሳየት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

በስልጠናው ላይ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እና አጎራባች ኦሮሚያ ክልል የተውጣጡ ከ4 መቶ በላይ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም