የማህበራቱን አደረጃጀት በማዘመን የአርሶና አርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመረው የሪፎርም ስራ ይጠናከራል - ኢዜአ አማርኛ
የማህበራቱን አደረጃጀት በማዘመን የአርሶና አርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመረው የሪፎርም ስራ ይጠናከራል
ሀዋሳ ፤ ሚያዝያ 20/2018(ኢዜአ)፦ የህብረት ስራ ማህበራትን አደረጃጀት በማዘመን የአርሶና አርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመረው የሪፎርም ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ህብረት ሥራ ኮሚሽን “ወደ ቀበሌ መድረስ” በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ ስድስት ከተሞች ሲያካሂድ የቆየውን 2ኛውን ሀገር አቀፍ የህብረት ሥራ ማህበራት ሪፎርም የንቅናቄ መድረክ ዛሬ አጠናቋል።
በሀዋሳ በተካሔደው የማጠናቀቂያ መርሃ ግብር ላይ የግብርና ሚኒስትሩ አዲሱ አረጋ በቪዲዮ ኮንፈረንስ ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት፤ ባለፉት ስምንት ዓመታት በተለያዩ መስኮች የበለጸገችና ህብረ ብሔራዊት ሀገር ለመፍጠር ዘርፈ ብዙ የሪፎርም ስራዎች ተግባራዊ ተደርገዋል።
በተከናወኑ ተግባራትም ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ ለውጦች እየተመዘገቡ መሆኑን አክለዋል።
የመንግስትን፣ የግሉ ዘርፍንና የዜጎችን የካፒታል አቅምና ዕውቀትን ደምሮ የሚይዙት የህብረት ስራ ማህበራት መሆናቸውን በግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲው በግልጽ መቀመጡን ጠቁመዋል።
ማህበራቱ ግብርናውን በማሻገር የአርሶና አርብቶ አደሩን ህይወት መቀየር ረገድ ትልቅ አቅም እንዳላቸው ገልፀው የፋይናንስ አቅርቦት ችግርን በመፍታትና የግብይት ሰንሰለቱን በማሳጠር የሸማቹን ህብረተሰብ ሸክም እንደሚያቀሉም አስረድተዋል።
በንቅናቄ መድረኩ የተሳተፉት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ህብረት ስራ ኤጀንሲ የህብረት ስራ ማህበራት ማደራጃና ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ ቶንጃ ቶማ በበኩላቸው፤ ማህበራቱ ገበያን በማረጋጋት፣ የአርሶ አደሩን ምርታማነት የሚያሳድጉ ግብዓት በማቅረብና በሌሎች ዘርፎች አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው ብለዋል።
በተለይ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የማህበራቱን አቅም ለማሳደግ በተደረገ የሪፎርም ስራ በኢኮኖሚው ውስጥ ያላቸው አበርክቶ እንዲያድግ ማድረጉን ተናግረዋል።
የኦሮሚያ ክልል ህብረት ስራ ልማት ኤጀንሲ ተወካይ ወይዘሮ ሹሬ እጅቢቾ፤ በክልሉ የህብረት ስራ ማህበራትን አሰራር፣ አደረጃጀትና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ በማተኮር ሪፎርም መሰራቱን ገልጸዋል፡፡
በዚህም ጠንካራ ማህበራት እንዲኖሩ አንድ ላይ የማደራጀት ስራ መሰራቱን ጠቅሰው በንቅናቄ መድረኩ የተገኘውን ልምድና እውቀት ተግባራዊ በማድረግ ለማህበራት ውጤታማነት እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡
የሲዳማ ክልል ህብረት ስራ ኤጀንሲ የህብረት ስራ ማህበራት ማደራጃና ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ ደምበሎ ዶንጊሶ በበኩላቸው፤ በሪፎርሙ የማህበራቱን ትርፋማነት፣ የአባላት ተጠቃሚነት ከማጎልበት አንጻር ለውጥ ማምጣት ተችሏል ብለዋል።
ከዚህም ባለፈ በአሰራር ስርዓት በአመራርና በአደረጃጀት የጠነከሩና የፋይናንስ አያያዛቸውን ያዘመኑ ማህበራት መፍጠር እንደተቻለ ገልጸው የተገኘውን ውጤት አጠናክሮ ለማስቀጠል የንቅናቄ መድረኩ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ነው የገለጹት።
ላለፉት ስምንት ቀናት በሀዋሳ ሲካሄድ በቆየው መድረክ ላይ ከሲዳማ፣ ከደቡብ ኢትዮጵያና ከኦሮሚያ ክልል የተውጣጡ 900 የቀበሌ ህብረት ስራ ማህበራት አደረጃጀት ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል።