የኢትዮጵያና የሞዛምቢክ ግንኙነት በነፃነት ትግል ወቅት በደም የተፈተነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያና የሞዛምቢክ ግንኙነት በነፃነት ትግል ወቅት በደም የተፈተነ ነው
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 20/2018(ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያና የሞዛምቢክ ግንኙነት በነፃነት ትግል ወቅት በደም የተፈተነ ታሪካዊ ወንድማማችነት ነው ሲሉ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ ገለጹ።
በኢትዮጵያ የሁለት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት የሞዛምቢክ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ዳንኤል ፍራንሲስኮ ቻፖ፣ በዛሬው ዕለት በኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር በመገኘት የሥራ ጉብኝት አድርገዋል።
ፕሬዝዳንቱና ከፍተኛ የልዑካን ቡድናቸው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሲደርሱ በሚኒስትሯ አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን፤ ከኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ጋርም ተወያይተዋል።
በዚሁ ወቅት ሚኒስትሯ የኢትዮጵያና የሞዛምቢክ ግንኙነት በነፃነት ትግል ወቅት በደም የተፈተነ ታሪካዊ ወንድማማችነት መሆኑን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ለሞዛምቢክ ነፃነት ያበረከተችው አስተዋጽኦ የፓን አፍሪካኒዝም መርህ ቀዳሚ መገለጫ መሆኑን አስታውሰዋል።
አሁን ያለውን ታሪካዊ ትስስር ወደ ላቀ ስልታዊ ወታደራዊ ትብብር ለማሸጋገርም ግልፅ ፍላጎትና ዕቅድ መኖሩን አመልክተዋል።
ፕሬዝዳንት ዳንኤል ፍራንሲስኮ ቻፖ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለሞዛምቢክ ሉዓላዊነትና ነፃነት ያበረከተችውን ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማስታወስ ምስጋና አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ያለውን የላቀ የውጊያ ብቃትና የዝግጁነት ደረጃ ያደነቁት ፕሬዝዳንቱ፣ ይህ ጉብኝት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግረው ገልፀዋል።
ፕሬዝዳንቱ በቆይታቸውም ከፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ጋር በወቅታዊ ቀጠናዊ የፀጥታ ጉዳዮችና በሁለትዮሽ ወታደራዊ ትብብር ስትራቴጂዎች ላይ ፍሬያማ ውይይት አድርገዋል።
ይህ የፕሬዝዳንቱ ጉብኝት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ስትራቴጂካዊ አጋርነት ከማጠናከሩ ባለፈ ለአህጉራዊ ሰላምና ደህንነት መጠናከር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው መገለጹን ኢዜአ ከመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።