ቀጥታ፡

የከተማዋ የአካባቢ ልማት ፕላን ቴክኖሎጂንና ፈጠራን በማስፋፋት የነዋሪዎችን ህይወት ለማሻሻል ያግዛል

አዳማ፤ ሚያዝያ 20/2018(ኢዜአ)፦የአዳማ ከተማ የአካባቢ ልማት ፕላን ቴክኖሎጂንና ፈጠራን በማስፋፋት የነዋሪዎችን ሕይወት ለማሻሻል ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር የከተማዋ አስተዳደር ከንቲባ ሃይሉ ጀልዴ ገለፁ።

የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከኦሮሚያ ከተሞች ፕላን ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የአካባቢ ልማት ፕላን ተፈፃሚነት  ዙሪያ በየደረጃው ካሉ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ መክሯል። 

የአካባቢ ልማት ፕላን (Local Development Plan - LDP) በአንድ በተወሰነ የከተማ ክፍል ወይም መንደር ውስጥ የሚከናወኑ የልማት ስራዎችን፣ የመሬት አጠቃቀም እና የመሰረተ ልማት ዝርጋታን በዝርዝር የሚመራ የከተማ ፕላን አይነት ነው።

የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሃይሉ ጀልዴ እንደገለጹት፤ የከተማዋ የአካባቢ ልማት ፕላን ቴክኖሎጂንና ፈጠራን በማስፋፋት የነዋሪዎችን ህይወት ለማሻሻል ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው።

ፕላኑ መሬትን በአግባቡ ለማስተዳደርና ለማልማት ካለው ፋይዳ በተጨማሪ ለከተማ ግብርና፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለቴክኖሎጂ ልማትና ስማርት አዳማ ኢንሼቲቭ ለማሳካት ተጨማሪ አቅም መሆኑንም ተናግረዋል።

የከተማ ፕላኑ የነዋሪውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለመመለስ እንደሚያግዝም ገልጸዋል። 

እንደ ከንቲባው ገለጻ፣ ፕላኑ ከዚህ በፊት የነበሩ የመልካም አስተዳደር እጦት ቅሬታዎችን፣ የመሬት አጠቃቀም ችግሮችና በመሰረተ ልማት ዝርጋታ ያሉ ማነቆዎችን በአግባቡ የፈተሸ ነው። 


 

የኦሮሚያ ከተሞች ፕላን ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሸለመ አበበ በበኩላቸው፣ ፕላኑ አዳማ ከተማ ሪጂኦ ከተማ ሆና የተደራጀችበትን ዓላማ የሚያሳካ መሆኑን ተናግረዋል።

የከተማዋን መዋቅራዊ ፕላን በማዘጋጀት ለመስተዳድሩ በማስረከብ ወደ ትግበራ እንደተገባ ገልጸው፣ የአካባቢ ልማት ፕላን መዋቅራዊ ፕላኑን ውጤታማ ለማድረግ ፋይዳው የላቀ ነው ብለዋል።

የአዳማ ከተማን ዕድገትን ለማሳለጥ የተከናወኑ የኮሪደር ልማትና ሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሰረተ ልማቶችን መሰረት በማድረግ መዋቅራዊ ፕላኑ መሰራቱንም ምክትል ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

በክልሉ የአዳማ፣ የቢሾፍቱና የሻሸመኔ ከተሞች በሪጂኦ ማዕቀፍ ውስጥ ሆነው ወደ ልማት ሥራ መግባታቸውን አንስተው የጂማ፣ ማያ፣ ሮቤ እና ነቀምት ከተሞች መዋቅራዊና የአካባቢ ልማት ፕላኖችም እየተዘጋጁ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም