ቀጥታ፡

የህብረት ሥራ ማህበራት ንቅናቄ ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግና ፋይዳው የጎላ ነው

ጅግጀጋ፤ ሚያዝያ 20/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የህብረት ስራ ማህበራት ሚና የጎላ መሆኑ ተገለጸ።

የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ማህበራት “ወደ ቀበሌ መድረስ” በሚል መሪ ቃል በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ሲያካሄድ የቆየው ሁለተኛው ሀገር አቀፍ የኅብረት ሥራ ሪፎርም ንቅናቄ ዛሬ ተጠናቀቀ።


 

በማጠቃለያ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት በኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን የህብረት ሥራ ቴክኖሎጂ ልማትና ማስፋፊያ መሪ ሥራ አስፈፃሚ እና የጅግጅጋ ማዕከል ንቅናቄ አስተባባሪ አንዱአለም አፈወርቅ እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን  የህብረት ሥራ ማህበራትን ለማጠናከር ያለመ  ሪፎርም እያካሄደ ነው። 

ለዚህም የንቅናቄ ስራን በሁለት ዙሮች  በማካሄድ  የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና በሚያረጋግጥ መልኩ እንዲንቀሳቀሱ ለማድረግ መሰራቱን  ገልጸዋል።

በዚህ ንቅናቄ  መድረኩ የተገኘውን እውቀት ወደ ተግባር በመቀየር በቀበሌ ደረጃ ያሉ ህብረት ሥራ ማህበራት በሪፎርሙ ታግዘው ህብረተሰቡን ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደርጉበትን አቅም ለመገንባት ይሰራል ብለዋል።

ንቅናቄው የህብረት ሥራ ማህበራት በሠው ሃይል፣ በፋይናንስና በቴክኖሎጂ የበለጸጉ እንዲሆኑ የሚያግዝ  መሆኑን  ጠቁመዋል። 

በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ከ360 በላይ ባለሙያዎች በዚህ በሁለተኛው ዙር የህብረት ሥራ ማህበራት ንቅናቄ መሳተፋቸውንም  ተናግረዋል።


 

በንቅናቄዉ ከተሳተፉ ባለሙያዎች መካከል አቶ ያህያ አህመድ በዚህ ቀበሌ የመድረስ ንቅናቄ ከፍተኛ ልምድ ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚህ የንቅናቄ ስልጠና የህብረት ሥራ ማህበራት ሪፎርም በአግባቡ ለመተግበር የሚያስችለንን እውቀት አግኝተናል ያሉት ደግሞ አቶ ሁሴን አህመድ ናቸዉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም