ቀጥታ፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅና በማላመድ የግብርና ምርታማነትን ማሳደግ ተችሏል 

ዲላ፤ ሚያዝያ 20/2018(ኢዜአ)፦በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅና በማላመድ የግብርና ምርታማነትን ማረጋገጥ መቻሉን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለፀ።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የይርጋጨፌ ግብርና ምርምር ማዕከል ግንባታ ማስጀመሪያ የመሠረት ድንጋይ የማስቀመጥ መርሃ ግብር ተካሄዷል።

ማዕከሉ ለጌዴኦ፣ ለቡርጂ፣ ለኮሬ ዞኖች የግብርና ምርምር በተለይም የቡና እና የእንሰት ምርታማነትን ለማሻሻል ትኩረት ተደርጎ እንደሚገነባም ተመላክቷል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ መሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት፤ በክልሉ ምርምርን መሠረተ ያደረገ የግብርና ልማትን በማረጋገጥ የአርሶ አደሩን ችግር ለማስወገድ እየተሠራ ነው።


 

በተለይ ቴክኖሎጂን በማፍለቅ፣ በማላመድና አዳዲስ የምርምር ሙከራዎችን በማከናወን ረገድ በርካታ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።

የቡና ዝርያ ለማሻሻልና አሰራርን ለማዘመን በተደረገ ጥረት በሞዴል አርሶ አደሮች ማሳ በሄክታር እስከ 20 ኩንታል የቡና ምርት ለማምረት መቻሉን ለአብነት ጠቅሰው ይህንን ማስፋት ዋናው የማዕከሉ ተልዕኮ ነው ብለዋል።

በተያዘው ዓመት ብቻ በሰብልና እንስሳት ጨምሮ በአምስት የግብርና ምርምር ዘርፎች 39 ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ መደረጉን ያነሱት ደግሞ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አብዮት መብራቴ (ዶ/ር) ናቸው።


 

የምርምር መሠረተ ልማትን በማስፋትና የተመራማሪዎችን ቁጥር በማሳደግ የግብርና ምርታማነትን ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ መሆኑን አንስተው የይርጋጨፌ የግብርና ምርምር ማዕከልም የዚሁ አካል ነው ብለዋል።

ማዕከሉ ለጌዴኦ፣ ለቡርጂና ለኮሬ ዞኖች በግብርና ምርምር በተለይም የቡና እና የእንሰት ምርታማነትን ለማሻሻል ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራም ተናግረዋል።

ይህም በክልሉ ሶስት ብቻ የነበሩትን የምርምር ማዕከላት የይርጋጨፌን እና የሳውላ ምርምር ማዕከላትን በመጨመር ወደ አምስት የሚያሳድግ ነው ብለዋል።

የይርጋጨፌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ቡኔ በበኩላቸው ፤በወረዳው ከ16 ሺህ 500 ሄክታር በላይ መሬት በቡና ልማት የተሸፈነ መሆኑን ገልፀዋል።


 

በወረዳው የቡናን ተፈጥሯዊ ጣዕም ጠብቆ ምርታማነቱን ለማሳደግ በተደረገ ጥረት በሞዴል አርሶ አደሮች ማሳ በሄክታር እየተገኘ ያለውን የከፍተኛ ምርት ተሞክሮ ለማስፋት የምርምር ማዕከሉ መገንባቱ ድርሻው የጎላ መሆኑንም አመልክተዋል።

የማዕከሉን ግንባታ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት እንደሚሰሩ ያረጋገጡት ደግሞ የክልሉ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አረጋ በዴቻ ናቸው።


 

ከ68 ሚሊዮን ብር በላይ የተመደበለት ማዕከሉ የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት የሚጠናቀቅ ሲሆን የአስተዳደር ህንጻ፣ ቤተሙከራ፣ የምርምር ማካሄጃ ስፍራዎችና መሰብሰቢያ አዳራሾችን ያካተተ መሆኑም ተገልጿል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም