ያገኘነውን ልምድና እውቀት ተጠቅመን ማህበራት የተሻለ ቁመና ላይ እንዲደርሱ ኃላፊነታችንን እንወጣለን-ሰልጣኞች - ኢዜአ አማርኛ
ያገኘነውን ልምድና እውቀት ተጠቅመን ማህበራት የተሻለ ቁመና ላይ እንዲደርሱ ኃላፊነታችንን እንወጣለን-ሰልጣኞች
ኮምቦልቻ ፤ ሚያዝያ 20/2018(ኢዜአ)፦ያገኘነውን ልምድና እውቀት ተጠቅመን የሕብረት ሥራ ማህበራት የተሻለ ቁመና ላይ እንዲደርሱ ኃላፊነታችንን እንወጣለን ሲሉ በኮምቦልቻ የሕብረት ስራ ሪፎርም ስልጠና ተሳታፊዎች ገለፁ።
የኢትዮጵያ ሕብረት ሥራ ኮሚሽን “ቀበሌ የመድረስ ምዕራፍ” በሚል መሪ ሃሳብ በኮምቦልቻ ሲያካሄድ የቆየው 2ኛው ሀገር አቀፍ የሕብረት ሥራ ሪፎርም የንቅናቄ መድረክና ስልጠና ዛሬ ተጠናቋል።
የስልጠናው ተሳታፊዎች ፤ ከስልጠናው ያገኘነውን እውቀትና ልምድ ተጠቅመን የህብረት ስራ ማህበራት የተሻለ ቁመና ላይ ሆነው ኢኮኖሚውን እንዲያነቃቁ ኃላፊነታችንን እንወጣለን ብለዋል።
ከተሳታፊዎቹ መካከል አቶ ሰለሞን እንቁዬ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ኮሚሽኑ የጀመረው ሪፎርም ባለሙያውን በማነቃቃት ገበያውን እያረጋጋ ኢኮኖሚውንም እያሳደገ ይገኛል።
ስልጠናው ህብረት ስራ ማህበራትን ለማጠናከር፣ ለማዘመን፣ የፋይናንስ ስርዓቱን ለማሻሻል፣ የፈጠራ ስራዎችንና አዳዲስ ሀሳቦችን በማዋሀድ በሪፎርሙ የተገኘውን ውጤት ለማስቀጠልና ለማጠናከር ያግዛል ብለዋል።
በዚህም ያገኘነውን ልምድና እውቀት ተጠቅመን ማህበራት የተሻለ ቁመና ላይ እንዲደርሱና ኢኮኖሚውን እንዲያነቃቁ የድርሻችንን እንወጣለን ብለዋል።
ሌላኛዋ ሰልጣኝ ማርታ ጌቱ በበኩላቸው፣ ስልጠናው የህብረት ስራ ማህበራትን እንቅስቃሴ በማጎልበት ለውጤት እንዲበቃ ሚናው የጎላ መሆኑን አመልክተዋል።
በተለይ ማህበራትን በአዲስ በማደራጀት፣ በቴክኖሎጂ በማስደገፍ፣ ካፒታላቸውን በማሳደግና የቁጠባ ባህላቸውን በማጠናከር ገበያውን እንዲያረጋጉና ኢኮኖሚውን እንዲያነቃቁ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል።
ማህበራት የተሻለ ቁመና ላይ እንዲደርሱ በተከናወኑ ተግባራት የተገኘውን አበረታት ውጤት አጠናክሮ ለማስቀጠል በቅንጅት እንሰራለን፣ ለዚህም ከስልጠናው እውቀትና ልምድ አግኝተናል ያሉት ደግሞ አቶ መሀመድ ሆላ ናቸው።
በተለይ ማህበራትን ከሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ጋር በማጣጣም የበለጠ ለውጤት እንዲበቁ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመው በኮምቦልቻ ከተማ ተዘዋውረን በመጎብኘት የልምድ ለውውጥም ማድረግ ችለናል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ህብረት ሥራ ኮሚሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊና የስልጠናው አስተባባሪ አቶ አምባዬ ወልዴ በበኩላቸው፤ ህብረት ስራ ማህበራትን በማጠናከር፣ በማዘመን፣ ካፒታላቸውን በማሳደግ፣ ትስስር እንዲፈጥሩና የላቀ ደረጃ እንዲደርሱ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ለዚህም አዲስ ሪፎርም ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራ መገባቱን አስታውሰው ኢኮኖሚውን በማነቃቃትና ገበያውን በማረጋጋት ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ገልጸዋል።
የበለጠ ለማጠናከርና ባለሙያውንም ለማነቃቃት በተለያየ ዙር ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመው በኮምቦልቻ ሲካሄድ የቆየው ስልጠናም ዛሬ መጠናቀቁን ገልጸዋል።
ከሚያዚያ 13 ቀን 2018 ዓ/ም ጀምሮ ሲካሄድ በቆየው ስልጠናና የንቅናቄ መድረክ የፌዴራል፣ የክልል፣ የዞንና የከተማ አመራሮች እንዲሁም የአማራና የአፋር ክልል የቀበሌ ህብረት ሥራ ማህበራት ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።