አዲስ አበባ ዓለም አቀፍ የብስክሌት ውድድር ልታስተናግድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ አበባ ዓለም አቀፍ የብስክሌት ውድድር ልታስተናግድ ነው
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 20/2018 (ኢዜአ)፦ ከመላው ዓለም የተውጣጡ የብስክሌት ተወዳዳሪዎች የሚሳተፉበት ሲቲ ማውንቴን ባይክ ኢሊሚኔተር (UCI City Mountain Bike Eliminator) ዓለም አቀፍ የብስክሌት ውድድር በአዲስ አበባ ሚያዚያ 24 እና 25 ቀን 2018 ዓ.ም ይደረጋል።
የዓለም አቀፉ የብስክሌት ህብረት (UCI) ዕውቅና የሰጠውና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተወዳጅነት ያተረፈው "ሲቲ ማውንቴን ባይክ ኤሊሚኔተር ፕሮ ሊግ" በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ፣ በኢትዮጵያ የሚካሄድ ይሆናል።
ውድድሩ በፒያሳ አድዋ ድል መታሰቢያ ዙሪያ የሚካሄድ ሲሆን፣ በዚህ ውድድር ከመላው ዓለም የተወጣጡ በርካታ ብስክሌተኞች እንደሚሳተፉ የከንቲባ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
ውድድሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለያዩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በቀጥታ የሚተላለፍ ሲሆን፣ ከ20 ሚሊዮን በላይ ተመልካቾች ይከታተሉታል ተብሎ ይጠበቃል።
በአዲስ አበባ የስፖርት መሰረተ ልማቶች መስፋፋት ከተማዋ ዓለማቀፍ ስፖርታዊ ውድድሮችን ለማካሄድ ተመራጭ ከተማ እንድትሆን ማድረጉን ጽህፈት ቤቱ ገልጿል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለትውልድ ግንባታ እና የስፖርት ዘርፍ ለኢኮኖሚ ግንባታ ያለውን ሚና እንዲጫወት ለማስቻል በቅርብ ዓመታት በርካታ የስፖርት መሰረተ ልማቶች እየገነባ እንደሚገኝም በመረጃው ላይ ተመልክቷል።