የፌዴሬሽን ምክር ቤት የቀድሞ አፈ ጉባኤ አምባሳደር ያለው አባተ የቀብር ስነ ስርዓት ነገ ይፈጸማል - ኢዜአ አማርኛ
የፌዴሬሽን ምክር ቤት የቀድሞ አፈ ጉባኤ አምባሳደር ያለው አባተ የቀብር ስነ ስርዓት ነገ ይፈጸማል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 20/2018 (ኢዜአ)፡- የፌዴሬሽን ምክር ቤት የቀድሞ አፈ ጉባኤ የአምባሳደር ያለው አባተ የቀብር ሥነ-ሥርዓት ነገ ሚያዝያ 21 ቀን 2018 ዓ.ም ይፈጸማል።
የቀብር ስነ ስርዓቱ ከቀኑ ስድስት ሰዓት ላይ በመንበረ ጸባኦት ቅድስተ ሥላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን እንደሚፈጸም ተገልጿል።
የአምባሳደር ያለው የቀብር ስነ ስርዓት ክብራቸውን በሚመጥን ሁኔታ ለማድረግ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየሰራ ይገኛል።
የአምባሳደሩ የአስከሬን ሽኝት ከቤታቸው ተነስቶ እስከ መንበረ ጸባኦት ቅድስተ ሥላሴ ካቴድራል ድረስ እንደሚካሄድም ተመላክቷል።
የቀብር ስነ ስርዓቱ የተለያዩ የፌደራል መንግሥት እና የክልል መንግስት ከፍተኛ አመራሮች፣ ቤተሰቦቻቸው እና ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት ይፈጸማል።
አምባሳደር ያለው አባተ ከአባታቸው አቶ አባተ ረታ እና ከወይዘሮ ተዋበች ፋንታሁን በቀድሞው ወሎ ክፍለ ሀገር በራያ እና ቆቦ አውራጃ ቆቦ ወረዳ ጉብዬ ከተማ መጋቢት 10 ቀን 1946 ዓ.ም ተወለዱ።
አምባሳደር ያለው በአማራ ክልል የክልሉ አፈ ጉባኤነትን ጨምሮ በተለያዩ የክልሉ ቢሮዎች በኃላፊነት አገልግለዋል።
በፌዴሬሽን ምክር ቤት ለሶስት ዓመታት ገደማ በአፈ ጉባኤነት የሰሩ ሲሆን በብራዚል የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነውም አገልግለዋል።
አምባሳደር ያለው አባተ ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በትናንትናው እለት በ72 ዓመታቸው ሕይወታቸው ማለፉ የሚታወስ ነው።