ቀጥታ፡

በዞኑ በመጪው ክረምት የሚተከሉ 275 ሚሊዮን ችግኞች እየተዘጋጁ ነው

መቱ ፤ ሚያዝያ 20/2018(ኢዜአ)፦በኢሉአባቦር ዞን በመጪው ክረምት በአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር የሚተከሉ 275 ሚሊዮን ችግኞች እየተዘጋጁ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዳሙ ታከለ ለኢዜአ  እንደገለጹት፤ ባለፉት ዓመታት በተካሔዱት የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር  እና የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ  ተራቁተው የነበሩ አካባቢዎች ማገገም ችለዋል።


 

በተጨማሪም ደርቀው የነበሩ ምንጮች መጎልበታቸውን በዘርፉ ከተመዘገቡ ውጤቶች መካከል ተጠቃሽ መሆኑንም ነው የተናገሩት ።

ይህንኑ በማጠናከር በመጪው ክረምት በአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር 275 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል የቦታ ልየታ ስራ እየተካሔደ መሆኑን ገልጸዋል።

በመርሐ -ግብሩ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ላላቸው የችግኝ ዓይነቶች ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሰራ ሲሆን ከዚህም ውስጥ የፍራፍሬ እና ለከብት መኖ የሚውሉ ችግኞችም ተጠቃሽ እንደሆኑ አንስተዋል።

የችግኝ ተከላ ስራው 62 ሺ ሔክታር መሬት ላይ  ይከናወናል ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው የተገለጸው።


 

አቶ ደረጀ ዓለሙና አቶ ምስጋና ከበደ በኖጳ ወረዳ በችግኝ ማፍላት ስራ ላይ መሰማራት በመቻላቸው ኑሯቸውን ለመደጎም የሚያስችል ገቢ እንዳስገኘላቸው ተናግረዋል።

አቶ ጥላሁን አለማየሁና ወንድሙ አሰፋ ደግሞ በግል የተለያዩ ችግኞችን በማዘጋጀትና ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ ለመሆን እየሰሩ መሆኑን ነው የገለጹት።

ባለፉት ዓመታት በተመሳሳይ ሁኔታ የፍራፍሬ ችግኞችን በማዘጋጀት እያቀረቡ ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታውሰው ለዘንድሮው ዓመትም የፓፓያ እና የአቮካዶ ችግኞችን እያዘጋጁ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም