በገበታ ለሸገር፣ ለሀገርና ለትውልድ መርሃ ግብሮች የተገነቡ የቱሪዝም መዳረሻዎች ዘርፉ ለሀገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ይበልጥ የሚያጎሉ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በገበታ ለሸገር፣ ለሀገርና ለትውልድ መርሃ ግብሮች የተገነቡ የቱሪዝም መዳረሻዎች ዘርፉ ለሀገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ይበልጥ የሚያጎሉ ናቸው
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 20/2018(ኢዜአ)፦ በገበታ ለሸገር፣ ለሀገርና ለትውልድ መርሃ ግብሮች የተገነቡ የቱሪዝም መዳረሻዎች ዘርፉ ለሀገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ይበልጥ የሚያጎሉ መሆናቸውን የቱሪዝም ሚኒስትር ሠላማዊት ካሳ ገለጹ፡፡
በየአካባቢው የሚገኙ የቱሪዝም ሀብቶችን ለማልማት በቅንጅት እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 17ኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል።
በምክር ቤቱ የአሠራርና የአባላት ሥነ-ምግባር ደንብ አንቀጽ 92 መሠረት የቱሪዝም ሚኒስትር ሠላማዊት ካሳ በምክር ቤቱ ተገኝተው ከአባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በውይይቱ ላይ አባላቱ በገበታ ለሸገር፣ ለሀገርና ለትውልድ መርሃ ግብሮች የተገነቡ አዳዲስ መዳረሻዎችን በማልማት የቱሪዝም ዲፕሎማሲን እና የኮንፈረንስ ቱሪዝምን ለማጠናከር የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማና አበረታች ናቸው ብለዋል፡፡
እነዚህ ሥራዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአካባቢ ጸጋዎችን ለይተው ወደ ሀብት ለመቀየር ያላቸውን ልዩ ክህሎትና ብቃት የሚያሳዩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ሀገራዊ የቱሪዝም መስህቦችን በመመዝገብ ረገድ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን የሚመለከትም ጥያቄ ቀርቧል።
ሚኒስትሯ በሰጡት ማብራሪያ፤ መንግሥት ቱሪዝምን አንዱ የኢኮኖሚ ምሶሶ በማድረግ የመዳረሻ ልማትን ጨምሮ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሐሳብ አመንጭነት በገበታ ለሸገር፣ በገበታ ለሀገር እና በገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች በርካታ የቱሪዝም ስፍራዎችና መዳረሻዎች መገንባታቸውን ጠቅሰዋል።
እነዚህ የልማት ሥራዎች ዘርፉ ለሀገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ይበልጥ የሚያጎሉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የመስህብ ምዝገባ ሂደትን በተመለከተም በሰጡት ማብራሪያም አበረታች በሆነ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው እስካሁንም 800 የሚሆኑ የቱሪስት መስህቦች መመዝገባቸውን ይፋ አድርገዋል።
በተጨማሪም ሀገር አቀፍ የቱሪዝም ካርታ በማዘጋጀት ረገድ በሲዳማ ክልል የተከናወነው የናሙና ሥራ በስኬት መጠናቀቁን ጠቅሰው ይህንን በመላ ሀገሪቱ የማከናወን ስራ የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ጠቁምዋል፡፡
የግሉ ሴክተር በየአካባቢው የሚገኙ የቱሪዝም ሃብቶችን በማልማት ሂደት ያላቸዉን ተሳትፎ ይበልጥ ለማጎልበት እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
እንዲሁም የማህበረሰቡን አቅም በማስተባበር የማልማት ስራ እና ደረጃቸውን ከፍ የማድረግ ስራዎች እንደሚሰሩም ጠቁመዋል፡፡