የባህር ዳር ስታዲየምን እስከ መጪው ሰኔ ወር መጨረሻ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተመላከተ - ኢዜአ አማርኛ
የባህር ዳር ስታዲየምን እስከ መጪው ሰኔ ወር መጨረሻ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተመላከተ
ባህር ዳር፤ ሚያዝያ 20/2018 (ኢዜአ)፡- የባህር ዳር ስታዲየምን እስከ መጪው ሰኔ ወር መጨረሻ ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ ለሀገር እና ለአህጉር አቀፍ ውድድሮች ዝግጁ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የአማራ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ገለፀ።
የቢሮው ኃላፊ መልካሙ ፀጋዬ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ የባህር ዳር ስታዲየም ታላላቅ የእግር ኳስ ውድድሮችን ማካሄድ እንዲችል ርብርብ እየተደረገ ነው።
ስታዲየሙ ሀገር አቀፍና አህጉር አቀፍ ውድድሮችን ለማካሄድ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (CAF) መስፈርቶችን መሰረት በማድረግ እየተሰራ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
በዚህም ካፍ እንዲስተካከሉ አስተያየት የሰጠባቸው የመጫወቻ ሜዳው ሣር፣ የክብር እንግዶች መቀመጫ ወንበሮች፣ የተጫዋቾች መልበሻ፣ የሚዲያና የህክምና ክፍሎች እንዲሁም መብራቶችና ሌሎችን ለማሟላት ሰፊ ስራ ተሰርቷል ብለዋል።
በመሆኑም ስታዲየሙን እስከ መጪው ሰኔ ወር መጨረሻ ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ ለውድድር ዝግጁ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በተጨማሪም የልምምድ ሜዳዎችና የመዋኛ ገንዳዎች ደረጃቸውን በጠበቀ አግባብ እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመው፤ መሟላት ያለባቸውን መስፈርቶች ለቅሞ በመያዝም አብዛኞቹ ስራዎች መጠናቀቃቸውን ጠቅሰዋል።
የተሟሉትን መስፈርቶች በተመለከተ የካፍ ገምጋሚ ቡድን በመምጣት የሚገመግመው ይሆናል ብለዋል።
ስታዲየሙ ወደ ውድድር ሲመለስ፤ ባህር ዳር ከተማና ፋሲል ከነማ በሜዳቸውና በደጋፊዎቻቸው ፊት እንዲጫወቱ እድልን ይፈጥራል ነው ያሉት።
እንዲሁም ታዳጊ ስፖርተኞችን በማነቃቃት ብቃት ያላቸውን ተተኪ ስፖርተኞች በሁሉም ዘርፍ ለማፍራትም የጎላ አስተዋጽኦ እንዳለው አመላክተዋል።