ቀጥታ፡

በዞኑ በበጋ መስኖ ተመርተው ለገበያ የቀረቡ ምርቶች ገበያን ማረጋጋት ችለዋል

ጎንደር፤ ሚያዝያ 20/2018 (ኢዜአ)፡- በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በበጋ የመስኖ ልማት ተመርቶ ለገበያ የቀረበ ከ4 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ገበያውን በማረጋጋት አስተዋጽኦ ማበርከቱን የዞኑ ግብርና መምሪያ ገለጸ።

በመምሪያው የመስኖ ልማት ቡድን መሪ ሀውልቱ ታደሰ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በዞኑ በበጋው ወራቶች ሁሉንም የውሃ አማራጮች በመጠቀም ከ48 ሺህ ሔክታር በላይ በመስኖ ማልማት ተችሏል፡፡


 

ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ15 ሺህ ሔክታር፤ የተገኘው ምርትም በ1 ሚሊየን ኩንታል ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል።

አርሶ አደሩ ገበያን መሰረት አድርጎ እንዲሠራ በተደረገለት ድጋፍና ክትትል መሰረትም፤ ጤፍ፣ ሩዝ፣ በቆሎ፣  ቲማቲም፣ ሽንኩርት፣ ድንችና ጥቅል ጎመን በማምረት ለገበያ ማቅረብ መቻሉን ገልጸዋል።

በአይነትም ሆነ በብዛት ተመርቶ ለገበያ የቀረበው ምርት የገበያ ዋጋን ከማረጋጋቱ ባለፈ፤ ሸማቹ ማህበረሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቶቹን እንዲያገኝ አስቻይ ሁኔታ መፍጠር ተችሏል ብለዋል።

አርሶ አደሩ ምርታማነትን የሚያሳድጉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችንና አሰራሮችን በስፋት በመጠቀም ለዘመናዊ የመስኖ ልማት መስፋፋት ትኩረት መስጠቱንም ገልጸዋል፡፡

በዚሁ ወቅት ለመስኖ አልሚ አርሶ አደሮች ከ4 ሺህ በላይ የውሃ መሳቢያ ሞተሮችን ጨምሮ ከ50 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በማቅረብ ለመስኖ ልማቱ ድጋፍ መደረጉን አስረድተዋል፡፡

በዞኑ የተገነቡ አነስተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ የመስኖ አውታሮችም አርሶ አደሩ ከዝናብ ጥገኝነት ተላቆ በዓመት እስከ ሶስት ጊዜ ማምረት የሚችልበትን እድል ፈጥረዋል ነው ያሉት።


 

አንደኛው ዙር የመስኖ ልማት ተጠናቆ ሁለተኛው ዙር መጀመሩን ጠቁመው በአሁኑ ወቅትም፤ ከ10 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት በመስኖ እየለማ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም