ቀጥታ፡

ረቂቅ አዋጁ በቁልፍ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን ለመመከትና ለመጠበቅ ያስችላል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 20/2018 (ኢዜአ)፡- የቁልፍ መሠረተ ልማቶች የሳይበር ደህንነት ረቂቅ አዋጅ በቁልፍ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን በመመከት ሉዓላዊነትን በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ እንዲቻል ያደርጋል ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ ምህረቱ ሻንቆ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 17ኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል።
 
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቁልፍ መሠረተ ልማቶች የሳይበር ደህንነትን ለማረጋገጥ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ለዝርዝር ዕይታ ለውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።
 
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ ምህረቱ ሻንቆ (ዶ/ር) የረቂቅ አዋጁን አስፈላጊነት አብራርተዋል። 
 
በዚህም በቁልፍ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚነጣጠሩ የሳይበር ጥቃቶች በሀገሪቷ ምጣኔ ሀብት፣ ማኅበራዊ መስተጋብር፣ ብሔራዊ ደህንነት፣ ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ሉዓላዊነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚፈጥሩ በመሆናቸው ረቂቅ አዋጁን ማዘጋጀት ማስፈለጉን ገልጸዋል።
 
በተጨማሪም በቁልፍ መሠረተ ልማቶች እና መሠረተ ልማቶቹ በሚይዟቸው ኢንፎርሜሽኖችና ዳታዎች ላይ እየጨመሩ የመጡ የሳይበር ደህንነት ተጋላጭነቶችና ሥጋቶችን መቀነስና መከላከል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ እንደሆነም አስረድተዋል።

ሥጋትን መሠረት ያደረገ የቁልፍ መሠረተ ልማቶች ልየታ በማድረግ የሀገሪቷን ሀብት አቀናጅቶ ለመምራት የሚያስችል የሳይበር ደህንነት ጥበቃና ቁጥጥር ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱም ነው ብለዋል።

ለቁልፍ መሠረተ ልማቶች የሳይበር ደህንነት ጥበቃ በባለድርሻ አካላት መካከል የተቀናጀ፣ ውጤታማና ፈጣን የመረጃ ልውውጥ እና የሳይበር ክስተቶችን ለማጋራትና ለመግታት የሚያስችል ሥርዓት መፍጠር አስፈላጊ ሆኖ ስለመገኘቱም አንስተዋል።

ውስብስብ፣ ተለዋዋጭ እና ከፍተኛ የሆነ ውድድር ባለበት የሳይበር ምህዳር ውስጥ የሚደረግ የሳይበር ደህንነትን የማረጋገጥ ተግባር ከፍተኛ የሆነ የካፒታል ዐቅምን የሚጠይቅ በመሆኑ ነው ብለዋል።
 
ለቁልፍ መሠረተ ልማቶች ጥበቃ የሚውል አስተማማኝ ሀገራዊ የፋይናንስ ዐቅም መፈጠር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ረቂቅ አዋጁ እንዲዘጋጅ ተደርጓል ነው ያሉት።

ቁልፍ መሠረተ ልማቶችን በሚያስተዳድሩና የሳይበር ደህንነት ጥበቃን በሚያደርጉ አካላት ላይ ግልጽ ኃላፊነትና ተጠያቂነት መፍጠር አስፈላጊ ሆኖ ስለመገኘቱም አክለዋል።

ምክር ቤቱ በስብሰባው፤ በኢፌዴሪ መንግሥት እና በፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ መካከል የተደረገ የብድር ስምምነት እና በኢፌዴሪ መንግሥት እና በአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ማኅበር መካከል የተደረገ የብድር ስምምነት ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ አፅድቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም