በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የኩታ ገጠም የቡና ልማት ውጤት አምጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የኩታ ገጠም የቡና ልማት ውጤት አምጥቷል
ዲላ፤ ሚያዝያ 20/2018 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በኩታ ገጠም የቡና ልማት የተገኘውን ስኬት ለማስፋፋት እየተሠራ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሠ መሥተዳድር እና የሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር) ገለጹ።
በጌዴኦ ዞን ዲላ ዙሪያ ወረዳ በሽጋዶ ቀበሌ የአረንጓዴ ዐሻራ የቡና ችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር ተከናውናል።
አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በአረንጓዴ ዐሻራ የተከናወኑ የልማት ሥራዎች የአፈር ለምነትን በማሻሻል በክልሉ የግብርና ምርታማነት አሳድገዋል።
በክልሉ የተጀመረው ቡናን በኩታ ገጠም የማልማት ሥራም በቡና ጥራትና ምርታማነት ላይ ውጤት ማምጣቱን ጠቅሰው፤ ተሞክሮን ለማስፋፋት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
ያረጀ የቡና ተክልን በተሻሻሉ የቡና ዝርያዎች በመተካት ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ፤ ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን የቡና መጠን ማሳደግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በተያዘው የበልግ ወቅት ከ40 ሚሊየን በላይ የተሻሻሉ የቡና ችግኞች ተከላ እየተከናወነ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በምክትል ርዕሠ መሥተዳድር ማዕረግ የግብርና ቢሮ ኃላፊ መሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር) ናቸው።
ከዚህ ውስጥ ከ5 ነጥብ 6 ሚሊየን የሚልቀው ችግኝ በኩታ ገጠም እንደሚለማ ጠቁመው፤ የቡና ጥራትና ምርታማነትን በማሻሻል የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተጀመሩ ሥራዎች ይጠናከራሉ ብለዋል።
በተያዘው ዓመት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃሐ-ግብር ቡናና ፍራፍሬን ጨምሮ የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸው ከ32 ሚሊየን በላይ ችግኞች ተከላ እየተካሄደ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) ናቸው።
የኩታ ገጠም የቡና ልማትን ለማስፋፋት በተደረገ ጥረት፤ 2 ሺህ 700 አርሶ አደሮችን በማሳተፍ ከ1 ሺህ 200 ሔክታር በላይ መሬት በኩታ ገጠም መልማቱን ገልጸዋል።
ዛሬ በዲላ ዙሪያ ወረዳ ሽጋዶ ቀበሌ የተካሄደው የቡና ተከላ መርሐ-ግብርም የዚሁ አካል መሆኑን ተናግረዋል።
የሽጋዶ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ዓለማየሁ ገብሬ፤ በአካባቢያቸው እየሰፋ የመጣው የኩታ ገጠም የቡና ልማት ልማዳዊ የቡና ልማትን በማስቀረት ምርታማነት እያሳደገ መሆኑን አንስተዋል።
ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር በኩታ ገጠም በሚያለሙት መሬት ከ1 ሺህ በላይ የተሻሻሉ የቡና ችግኞችን መትከላቸውንም አስረድተዋል።
ከቡና በተጨማሪ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚደርሱ ቦሌቄ፣ እንሰትና ሌሎች ሰብሎችን በመትከል ተጠቃሚ ለመሆን እየሠሩ መሆናቸውንም አመልክተዋል።